Search

የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ በፈጠራ፣ በፍጥነት እና በጥራት መሥራት ለሁለንተናዊ ብልፅግና መረጋገጥ አስፈላጊ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

እሑድ ጥቅምት 30, 2018 294

የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ በፈጠራ፣ በፍጥነት እና በጥራት መሥራት ለሁለንተናዊ ብልፅግና መረጋገጥ አስፈላጊ እንደሆነ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት እና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
"በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሐሳብ ከፌዴራል፣ ከክልል፣ ከዞን እንዲሁም ከከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለተከታታይ 11 ቀናት ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ተጠናቅቋል።
የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት እና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ላይ የማጠቃለያ ሥልጠና ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማጠቃለያ ሥልጠና ላይ እንደገለጹት የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ በፈጠራ፣ በፍጥነት እና በጥራት መሥራት ለሁለንተናዊ ብልፅግና መረጋገጥ አስፈላጊ ነው።
በሥልጠናው የመደመር መንግሥት ፅንሰ ሐሳብ፣ መንገድ እና መዳረሻ ግቦቹ ተዳስሰዋል።
በዚህም በመደመር መንግሥት መርሕ የሚመራው የፓርቲው አመራሮች በፈጠራ፣ በፍጥነት እና በብዛት ሥራዎችን በማከናወን የሕዝቡን ሁለንተናዊ ጥያቄ ከመመለስ በላይ የሀገሪቱን ራዕይ ለማሳካት እና ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚረዳ መንገድ መምራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት የሚሹ ግቦችን በየፈርጁ በመለየት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በዚህም ፋይዳ፣ 5 ሚሊዮን ኮደሮች፣ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች፣ የምርጫ ምቹነት እና የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም አጀንዳዎችን መቶ በመቶ ለማሳካት መትጋት የሚገባን ግቦች ናቸው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ መደመር ትውልድን ወደ ብልፅግና የሚያደርስ መንገድ መሆኑን አብራርተዋል።
የመደመር መንግሥት ለሀገር ብልፅግና ባለአደራ መሆኑንም ተናግረው በፈጠራ እና በፍጥነት ጥራት እና ብዛትን እውን ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በብዝሀ ዘርፍ ትሥሥር ወደ ስልጣኔ ሽግግር ማምጣት እንደሚገባም ማብራራታቸውን የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።
የሐሳብ ሉዓላዊነት የብልፅግና መሠረት እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሁሉም የፓርቲው አመራር በዚህ አግባብ በመትጋት ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ አለበት ብለዋል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ባለፉት 11 ቀናት በሥልጠና በውይይት እና በመስክ ጉብኝት፣ በማጠቃለያው ገለጻ ያገኟቸውን እውቀት አና ልምዶች በዕቅድ በማካተት እና ወደ ሥራ በመቀየር የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።