Search

ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ስለ ባሕር በር ምንድን ነው ያሉት?

ማክሰኞ ኅዳር 02, 2018 372

የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ የባሕር በር ጉዳይ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሊፈጥር ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ።

ለ100 ዓመታት ያህል በጎረቤት ሀገር ወደብ ላይ ጥገኛ የሆነችው ኡጋንዳ ወደብ አልባ መሆኗ በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑን የገለፁት ሙሴቬኒ፤ ይህ ጥገኝነት የቀጣናውን ሰላም ሊያናጋ የሚችል አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

አያይዘውም፥ “የባሕር በር ያላቸው ሀገራት መተላለፊያውን በብቸኝነት ለመያዝና ለመቆጣጠር መፈለጋቸው ጤነኝነት አይደለም” ብለዋል።

ኡጋንዳ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ ከኬንያው የሞምባሳ ወደብ ላይ ጥገኛ ሆና ቆይታለች። በዚህም ሀገሪቱ ከፍተኛ ለሆነ ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ስትዳረግ የቆየች ሲሆን፤ በዓመታዊ የዕድገት ምጣኔዋ ላይም በአማካይ የ1.5 በመቶ ቅናሽ እያስከተለ ቆይቷል።

ኡጋንዳ በዚህ ወደብ ጥገኛ በመሆኗ የተነሳ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ሲሆን፤ ወደ ውጭ የሚላኩ የኡጋንዳ ምርቶችም በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ምክንያት ሆኗል።

ከዚህም ባሻገር የኡጋንዳ ወደብ አልባ መሆን እና አማራጭ የባሕር በር አለመጠቀሟ  በጎረቤት ሀገራት የሚከሰቱ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች በሀገሪቱ ላይ ጉዳት እንዲደርሱ እያደረገ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2007/2008 በኬንያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በሀገሪቱ አለመረጋጋት በተከሰተበት ወቅት ችግሩ ድንበር ተሻግሮ የኡጋንዳን ኢኮኖሚ ማናጋት መጀመሩ አይዘነጋም።

የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በኬንያ በተከሰተው ሁከት ምክንያት የሞምባሳ ወደብን ከኡጋንዳ ጋር የሚያገናኙት ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተው በሺዎች የሚቆጠሩ ኮንቴይነሮች እና የነዳጅ ማጓጓዣዎች በወደብ እና በመንገድ ላይ በመቅረታቸው ነበር።

በኬንያ ለወራት የዘለቀው አለመረጋጋት በኡጋንዳ የነዳጅ እና ሌሎች አስፈላጊ ሸቀጦች እጥረት እንዲከሰት በማድረጉ ዋጋቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚም ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዷል።

ከዚህ ክስተት በኋላ ኡጋንዳ ከሞምባሳ ወደብ በተጨማሪ የዳሬሰላም (ታንዛኒያ) ወደብንም እንደ አማራጭ የንግድ መስመር በስፋት መጠቀም ጀምራለች። ይህም አንዱ መንገድ ሲዘጋ ሌላኛውን ለመጠቀም እንደሚያስችላት ታምኖበታል።

ይሁን እንጂ ከ100 ዓመታት በላይ በኬንያው የሞምባሳ ወደብ ስትጠቀም የቆየችው ኡጋንዳ ለኢኮኖሚዋ አለመረጋጋት ዋንኛው መንስኤ እየሆነ በመጣው የወደብ ጥገኝነት ምክንያት ኢኮኖሚዋን ሊደግፍ የሚችል ገንዘብ እያጣች መሆኑ አሳስቧታል።

እናም ፕሬዚዳንቷ የባሕር በር ጉዳይ በአንድ አፍሪካዊ ወንድማማችነት ፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ መፈታት እንዳለበት በተለያዩ ወቅቶች ጠይቀዋል።

ይህ ካልሆነ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የሚያጋጥማቸው ችግር ቀጣናዊ መልክ መያዙ እና የቀውስ ምንጭ መሆኑ እንደማይቀር ነው የሚናገሩት።

ችግሩን ለመከላከል የባሕር በር ያላቸው ሀገራት በጋራ የመበልፀግ መርሕን በመከተል የባሕር በር ለሌላቸው ሀገራት ነፃ የመተላለፊያ መብት መስጠት እንዳለባቸው ነው የገለጹት።

በዋሲሁን ተስፋዬ