እየተገባደደ በሚገኘው 30ኛው የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ (cop30) ከስምምነት ለመድረስ የሚያስችሉ ጉዳዮችን አስመልከቶ ኢትዮጵያ አቋሟን አንፀባርቃለች።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ ስዩም መኮንን፥ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ የሆኑ ተግባራትን በስፋት አከናውናለች፣ ይህንንም አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
ለችግሩ ጉልህ አስተዋጽኦ ሳይኖራት በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሆነችው አፍሪካ የመፍትሔው መፍለቂያ በመሆን ግን ቀዳሚ ናት ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እውቅና ያስገኙላትን ሥራዎች ግንባር ቀደም ሆና መፈፀሟን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በ2030 የደን ሽፋኗን 30 በመቶ ለማድረስ እየሠራች መሆኗን ያነሱት አቶ ስዩም፤ ከካርቦን ልቀት የተላቀቀ ኢኮኖሚን ለመገንባት የኃይል ሽግግሯን እያሳለጠች እንደሆነም ነው የገለጹት።
የተቀናጀው የኮሪደር ልማት ሥራም ከተሞችን እየለወጠ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴዔታው፤ ሀገሪቱ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናዋን እያረጋገጠች ነው ብለዋል።
32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ እንድታስተናግድ ዓለም ኢትዮጵያን በመምረጥ ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለወሰደችው ተጨባጭ እርምጃ እውቅና የሰጠበትም ነው ብለዋል።

አፍሪካም እንደ አህጉር መሰል አዎንታዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን ታረጋግጣለች ሲሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የተካሄደው 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ውጤታማ እንደነበር ያነሱት አቶ ስዩም፤ ሀገሪቱ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔንም በስኬት ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ጉባዔው፣ አፍሪካ የመፍትሔው አካል መሆኗን ወደ አረጋገጠችው ኢትዮጵያ መምጣቱም ትክክለኛ እና ተገቢ ነው ብለዋል።
የዓለም የሙቀት መጠንን ከ1 ነጥብ 5 እስከ 2 ዲግሪ ሴልሺየስ እንዳይበልጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ለትግበራው የሚጠቅመውን የገንዘብ ድጋፍ በወቅቱ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ በአፅንዖት ተናግረዋል።
የብራዚሉ ኮፕ 30፣ ከቃል ይልቅ ተግባር የሚንፀባረቅበት፣ ፍትሕም የሚረጋገጥበት እንዲሆን ጥሪ አቅርበው፤ ኢትዮጵያ እስከአሁን እንደሠራችው ሁሉ የበኩሏን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
በብራዚል ቤሌም እየተካሄደ የሚገኘው ጉባዔው በቀጣይ ቀናት ዋና ዋና ውሳኔዎቹን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በሀብታሙ ተክለሥላሴ
#ebcdotstream #cop30 #brazil #belem #ethiopia