Search

በአማራ ክልል የመስኖ ልማት እንዲስፋፋ ግብርና ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል - አቶ አዲሱ አረጋ

ማክሰኞ ኅዳር 16, 2018 83

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ደዋ ጨፋ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

በመርሐ ግብሩ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እንዲሁም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋን (ዶ/ር) ጨምሮ የፌደራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ፥ ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበች እንደሆነ ገልጸዋል።

በተያዘው ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ከ175 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየተሠራ ነው ብለዋል።

እስከአሁን ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸው፤ የዛሬው የመስክ ጉብኝት በክልሉ የመስኖ ልማት ሥራዎችን ለመከታተል እና ለመደገፍ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ክልሉ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሳይበገሩት በግብርናው ዘርፍ እያሳየው ያለው ውጤት አበረታች ነው ያሉት አቶ አዲሱ፤ የግብርና ሚኒስቴርም አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፥ በዚህ ዓመት በክልሉ ከ350 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ በመሸፈን ከ13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አህመድ አሊ፥ በአስተዳደሩ ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ የግብርና ሜካናይዜሽንን ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

ዛሬ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በተጀመረበት ደዋ ጨፋ ወረዳ፣ ጎበያ ቀበሌ ስንዴን በኩታገጠም የዘሩ አርሶ አደሮች፤ ከዚህ ቀደም እንደዋዛ ያሳለፉት ጊዜ እንደሚቆጫቸው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የጤፍ ሰብላቸውን ሰብስበው የበጋ መስኖ ስንዴን እየዘሩ ይገኛሉ።

ከወራት በኋላ ስንዴውን በመሰብሰብ ሌላ ሰብል ዘርተው በዓመት አንዴ ከማምረት ሦስቴ ወደማምረት ለመሸጋገር ዕቅድ ይዘዋል።

ከራሳቸው የምግብ ፍጆታ አልፈው ለገበያ ለማቅረብ ማቀዳቸውንም ነው አርሶ አደሮቹ የገለጹት።

#ebcdotstream #Ethiopia #AmharaRegion #Wheat