የጋናው ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ለአፍሪካ እውነተኛ ነፃነት የፖለቲካ ነፃነት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ ግስጋሴ ላይ ገደብ የሆኑ አዳዲስ እና ውስብስብ ኃይሎች ያሏቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ቴክኖሎጂያዊና ርዕዮተ-ዓለማዊ ጉዳዮች መጋፈጥ የግድ መሆኑን አሳስበዋል።
በ‘ፓን አፍሪካን ፕሮግሬሲቭ ፍሮንት’ ጉባዔ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ማሃማ፥ ቅኝ ገዥነትን በማስወገድ የተገኙት ታሪካዊ ድሎች ራስን በራስ የማስተዳደርን በር ቢከፍቱም፤ "እውነተኛ ነፃነት ግን ከዚህ የበለጠ ብዙ ሥራ ይጠይቃል" ብለዋል።

አፍሪካ በሐብቷ የበለፀገች ሆናም በዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ድሃ መሆኗን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ አዲሱ የፓን አፍሪካን ትግል የኢኮኖሚ ለውጥ፣ ቴክኖሎጂያዊ ሉዓላዊነት፣ የአየር ንብረት ፍትሕ እና ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓትን ለማረጋገጥ መሆን አለበት ነው ያሉት።
በአህጉር አቀፍ ውህደት ዙሪያ ብዙ ንግግር ቢደረግም፣ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ገና ከ20 በመቶ በታች ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱዕ ይህን ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የዛሬው ትግል “ቅኝ ግዛትነትን ከመዋጋት ትግል ይልቅ ውስብስብ እና ፈታኝ ነው” በማለት ትግሉን በድል መወጣት ለአፍሪካ ክብር እና ብልፅግና ወሳኝ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
በሰለሞን ገዳ
#ebcdotstream #panafricanism #ppf #Mahama