Search

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ብትወጣ ለቀጣናው ሠላም የበለጠ ትሠራለች - የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል

ማክሰኞ ኅዳር 16, 2018 92

ኢትዮጵያና አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ።
የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ (U.S. Africa Command - AFRICOM) አዛዥ በሆኑት ጄኔራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን የተመራ ልዑክ ከኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ ላይ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የቀጠናው ሀገራት በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ተመላክቷል።
 
ሁለቱ ሀገራት በወታደራዊ እና በተለያዩ መስኮች ለበርካታ ዓመታት በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን ያነሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ኢትዮጵያ ፀረ-ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ ገልፀዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ አልሸባብን ለማዳከምና የሽብር ሴራውን ለማክሸፍ የምትወስደውን የኃይል እርምጃ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን አስመልክተው ሲያብራሩም፤ የሀገሪቱ ፍላጎት ለሰላማዊ አገልግሎትና ኢኮኖሚን ለመገንባት መሆኑን በመጥቀስ፣ ከአሜሪካ ጋር ያለው ወታደራዊ ግንኙነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለልዑካን ቡድኑ አስረድተዋል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ፀጥታን ለማስፈን እየተጫወተች ያለውን ሚና አድንቀው፣ ሽብርተኝነትን በጋራ የመዋጋት ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሠላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን መንገድ እንደሚደግፉ የገለፁት የአሜሪካው ጄነራል፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ብትወጣ የበለጠ ለቀጣናው ሠላም ትሠራለች ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ በኩል ያሉ ፍላጎቶችንና በቀጠናው ሠላምን ለማረጋገጥ ስለያዘቻቸው ዕቅዶች ከዋሽንግተን ዲሲ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩም ጠቁመዋል።
በዕለቱ "የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ሁኔታ" በሚል ርዕስ በኮሎኔል መስፍን አውላቸው ጥናታዊ ፅሑፍ ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ መሪዎች ስጦታ መለዋወጣቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ መረጃውን አድርሶናል።