በአፋር ክልል አፍዴራ ወረዳ በሚገኘው የኤርታሌ እሳተ ገሞራ አካባቢ በትናንትናው ዕለት የተከሰተው ፍንዳታ ከዚህ ቀደም ከታዩት ፍንዳታዎች የተለየ እንደነበር ተገልጿል።
ይህንን ክስተት ተከትሎም የኢቢሲ ጋዜጠኛ ቡድን ወደ ስፍራው በመጓዝ በኤርታሌ እሳተ ገሞራ አካባቢ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተመልክቷል።
ኅዳር 14 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ሰዓት ከሰመራ ተነስቶ ጉዞ የጀመረው የጋዜጠኛ ቡድን ምሽት 12:30 ላይ አፍዴራ ከተማ ሲደርስም የወረዳውን ነዋሪዎች ስለ ሁኔታው ጠይቋል።

ነዋሪዎቹም ትናንትና ከጠዋቱ 4:00 ጀምሮ የተከሰተው ፍንዳታ በአካባቢው ላይ የመሬት ንዝረት፣ ጭስ እና ብናኝ እንደፈጠረ ገልጸው፣ ክስተቱ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ እንደሆነ ተናግረዋል።
ቡድኑ ምሽት 3:30 ላይ እሳተ ገሞራው ወደሚገኝበት ስፍራ ሲደርስ፣ ቀን ላይ ሕዝቡን ሲያጨንቅ የነበረው ፍንዳታ እና ጭስ ረገብ ብሏል፣ አስጎብኚዎችም ቱሪስቶችን ለተጨማሪ ጉዞ በማስተባባር ላይ ነበሩ።
ምሽት ላይ ክስተቱን በግልጽ ማየት የማይቻል ስለነበር ቡድኑ አዳሩን በኤርታሌ ተራራ ስር አድርጎ ማለዳ ላይ ከአስጎብኝዎች ጋር ወደ ተራራው ወጥቷል።
በዚህ ወቅትም ከዚህ ቀደም በእሳት ባህርነት (Lava Lake) የሚታወቀው የኤርታሌ እሳተ ገሞራ ደርቆ፣ እንደ አዲስ ለመፈንዳት የሚያደርገው እንቅስቃሴ እና ድምፅ እየተሰማ ነበር።
ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ የነበረው የእሳት ባህሩ ደርቆ ትላልቅ አለቶችን መፍጠሩ እና የተፈጠሩት ተራራዎችም ወደ ውስጥ ሸለቆ እየሰሩ እየተናዱ መገኘታቸው ነው።

እሳተ ገሞራው ከዚህ ቀደም ይታወቅ የነበረው በኤርታሌ ተራራ ላይ ቢሆንም፤ ትላንት የተፈጠረው አዲሱ ፍንዳታ ግን ''ሃይሌ-ጉብ'' በሚባለው ሌላኛው ትልቅ ተራራ ላይ የተከሰተ ሲሆን፣ በኃይል እየጨሰ እና ተራራውም እየተናደም ይገኛል።
በአዲሱ ተራራ ላይ የተከሰተው ፍንዳታ አስፈሪ ቢሆንም፣ በሌላ መልኩ ደግሞ ለቱሪስቶች የሚስብ ትዕይንትን ፈጥሯል።
ሆኖም ወደ አዲሱ ስፍራ የሚወስድ ምቹ መንገድ ስለሌለ ጎብኚዎች ከኤርታሌ ተራራ ላይ ሆነው ክስተቱን ለመመልከት ተገደዋል። በአካባቢው የሚገኙ ቱሪስቶችም ይህን የተፈጥሮ ክስተት ለማየት እየተንቀሳቀሱ ይገኛል።
የኤርታሌ እሳተ ገሞራ በየጊዜው በተለያዩ ወቅቶች የሚቀንስ እና እንደ አዲስ እየፈነዳ የሚከሰት መሆኑን የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ሀሰን ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው መረጃ ከሆነ አሁን የሚታየው ፍንዳታ በየጊዜው በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሲከሰት የነበረ እና አሁን የተከሰተውም ወቅቱን የጠበቀ ነው። ሆኖም እንዲህ አይነት ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሲፈጠሩ አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
በሁሴን መሀመድ