Search

የጋርዲዮላ ደቀ መዛሙርት በአውሮፓ ትልቁ መድረክ አርሰናል ከ ሙኒክ

ረቡዕ ኅዳር 17, 2018 23

ከስፔናዊው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ብዙ ነገር ወስደው ደግሞም የራሳቸውን ጨምረውበት በዚህ የውድድር ዓመት በሀገር ውስጥም ይሁን በአህጉር አቀፍ መድረክ እጅግ አስፈሪ ቡድን ገንብተው አሳይተዋል፡፡ ሚካኤል አርቴታና እና ቪንሰንት ኮምፓኒ፡፡ ሁለቱ አሰልጣኞች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 5ኛ ዙር ጨዋታ ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት ላይ በኤምሬትስ የሚገናኙበት ጨዋታ ትልቅ ግምት አግኝቷል፡፡
 
አርሰናል እና ባየር ሙኑክ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ያደረጓቸውን አራቱንም ጨዋታዎች አሸንፈዋል፡፡ በሌላ በኩል በውስጥ ውድድሮች የሊጉ መሪዎች ናቸው፡፡ የወቅቱ የአውሮፓ ብቻ ሳይሆን የዓለም ምርጥ ቡድኖች የሚገናኙበት ጨዋታ ደግሞ በብዙ መልኩ የሚጠበቅ ሆኗል፡፡
 
በእርግጥ በሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነት የጀርመኑ ክለብ ትልቅ ብልጫ አለው፡፡ ዛሬ ምሽት በመድረኩ ለ15ኛ ጊዜ የሚገናኙበት ጨዋታ ግን ከባለፉት ዓመታት ፍጹም የተለየ መልክ አለው፡፡አርሰናል በዚህ ዓመት በሻምፒዮንስ ሊጉ ያደረጋቸውን አራቱንም ጨዋታዎች ማሸነፉ ብቻ ሳይሆን አንድም ግብ ያልተቆጠረበት ብቸኛ ክለብ ነው፡፡
 
ባየር ሙኒክ በመድረኩ ሦስት ግቦች ቢቆጠሩበትም የፊት መስመሩ ግን ከአርሰናልም የበለጠ አስፈሪ ነው፡፡ በሀሪ ኬን የሚመራው የአጥቂ ክፍል 14 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፡፡
 
በምሽቱ መርሀ ግብር እንግሊዛዊው አጥቂ ከጠንካራው የመድፈኞቹ ተከላካይ የሚጠብቅውን ፈተና እንዴት ይወጣዋል የሚለው ሌላኛው የሚጠበቅ ጉዳይ ሲሆን ከአርሰናል በተገናኝባቸው 21 ጨዋታዎች 15 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ስድስቱ ኤምሬትስ ላይ ያስቆጠራቸው ሲሆኑ ኤምሬትስ ላይ የእሱን ያክል ግብ ያስቆጠረ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋች የለም፡፡
 
በፕሪሚያር ሊጉ በሊቨርፑል 1 ለ 0 ከተሸነፉ በኋላ ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ያልተሸነፈው የሚካኤል አርቴታ ቡድን በሳምንቱ መጨረሻ በሰሜን ለንደን ደርቢ የሀሪ ኬንን የቀድሞ ክለብ ቶተንሀምን 4 ለ 1 አሸንፎ ነው ለሌላኛው ከባድ ፈተና የተዘጋጀው፡፡
 
ባቫርያኑ ደግሞ በሁሉም ውድድሮች ካደረጓቸው 18 ጨዋታዎች 17ቱን ሲያሸንፉ በሊጉ ነጥብ የተጋሩት ከኡኒየን በርሊን ጋር ብቻ ነው፡፡ በቡንደስ ሊጋው በሳምንቱ መጨረሻም ፍራይበርግን 6 ለ 2 አሸንፈዋል፡፡
 
ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ ተጋጣሚዎቻቸውን ባሸነፉበት ጨዋታ የቀድሞዎቹ የክሪስታል ፓላስ ተጫዋቾች ኤቤሬቺ ኤዜ እና ሚሼል ኦሊሴ የደመቁበት ሆኖ አልፏል፡፡ የቡድኖቻቸው ቁልፍ ተጫዋች የሆኑት ሁለቱ ከዋክብት ዛሬ በተቃራኒ ለአሸናፊነት የሚፋለሙበት ሌላኛ የሚጠበቀው ይሆናል፡፡
 
ጋብርኤል ማጋሌሽ፣ ቪክቶር ዮኬሬስ እና ማርቲን ኦዴጋርድ አሁንም ነጉት መድፈኞቹን የማያገለግሉ ሲሆን ማርቲኔሊ ግን ለጨዋታው ዝግጁ ነው፡፡

 

በአንተነህ ሲሳይ