በተባበሩት ዐረብ ኤሚሬቶች የኢፌዲሪ ልዩ መልእክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር)፣ የዲፒ ወርልድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከሆኑት ሱልጣን አህመድ ቢን ሱላዬም ጋር በኢትዮጵያና በኩባንያው መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ያለመ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የንግድና ሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ በመንግሥት እየተወሰዱ ባሉ ተግባራት እና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ ለዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ሰጥተዋል።
በተለይም በደረቅ ወደብ ልማት፣ በሎጂስቲክስ መሠረተ ልማት ማስፋፋት እና ማዘመን እንዲሁም የንግድ ኮሪደሮችን ብዝሃነት በማስፋት ዙሪያ ኢትዮጵያ ከኩባንያው ጋር ይበልጥ በአጋርነት በመሥራት በቀጠናው የገቢና ወጪ ምርቶች ዝውውርን ለማቀላጠፍ በትኩረት እየሠራች መሆኗን አስታውቀዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ እና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ያሉት አምባሳደሩ፣ ውጥኑን ከግብ ለማድረስ በዘርፉ የላቀ ልምድ ካለው ከዲፒ ወርልድ ጋር ያላትን የአጋርነት አድማስ በማስፋት በትብብር መሥራቷን እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
የዲፒ ወርልድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሱልጣን አህመድ ቢን ሱላዬም በበኩላቸው፤ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ የሚያደርገው ኢንቨስትመንት ዘላቂና ለቀጠናው ማኅበረሰብ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።
በጋራ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በማፋጠን ኢትዮጵያ የቀጠናው የሎጂስቲክስ ማዕከል ለመሆን የጀመረችውን ጥረት እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡
በውይይቱ መጨረሻ ሁለቱ የሥራ ኃላፊዎች በቅንጅት ለመሥራት፣ እንዲሁም በዲጂታል ሎጂስቲክስ፣ በአቅርቦት ሰንሰለት ዝርጋት እና በነፃ የኢኮኖሚ ዞኖች ግንባታ ዙሪያ ያሉ አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለመቃኘት መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡