Search

የቅቤ ዕቁብ ባህል በጉራጌ

በተለምዶሰውን ሰው ያደረገው ዕቁብ ነውሲባል እንሰማለን።

ባህላዊ የቁጠባ መንገድ የሆነው ዕቁብ፤ በተለምዶ የገንዘብ ብቻ እንጂ በሌላ መልኩ ሊከወን ይችላል ተብሎ ቢነገር ላያሳምን ይችል ይሆናል።

የቅቤ ዕቁብ በአብዛኛው የጉራጌ አካባቢዎች የተለመደ ሲሆን፤ በእነሞር ወረዳ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረው የቅቤ ዕቁብ፣ ዕቁብ ከገንዘብ አልፎ እንደሚከወን ማሳያ ነው።

ዕቁቡ፥ በዓላት፣ ቤተሰባዊ ሁነቶች፣ ድንገተኛ ሀዘን መሰል ክስተቶች ሲፈጠሩ ለሚዘጋጁ ምግቦች ግብዓት የሆነው ቅቤ ከጓዳ እንዳይታጣ በማለት 4 ሴት ጓደኛሞች የተጀመረ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የቅቤ ዕቁቡ ያለው ጥቅም ቀላል አለመሆኑን ከጎረቤቶቻቸው ያዩ ሌሎች ነዋሪዎችም ዕቁቡን እንደተቀላቀሉና የአባላት ቁጥር ከፍ እያለ መምጣቱንም ያስረዳሉ።

እያንዳንዳቸውም የሚያመጡት ትንሽ መጠን ያለው ቅቤ በአንድ ሲሆን ሚዛን የሚደፋ ይሆናል ይላሉ። 

ይህም  ዝግጅቶች ሲኖሩ በአቅም ማነስ ምክንያት የቅቤ እጥረት እንዳይኖር አንዱ ለአንዱ የሚሰጥበት እያለ ሁሉም በዚህ መልኩ ተጠቃሚ የሚሆኑበት መሆኑን ያስረዳሉ።

ችግርን አጉልቶ ከማዘን፡  መፍትሄ ማበጀት መልካም እንደሆነ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፤ የዕቁብ ሥነ-ስርዓቱ ጓዳን ከመሙላት ባሻገር እንደ አንድ አካባቢ ነዋሪ የሚጠያየቁበት፣ ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን የሚያደምቁበት ብሎም ስለተለያዩ ጉዳዮች ሃሳብ የሚለዋወጡበት መሆኑን ተናግረዋል።

በአፎሚያ ክበበው