Search

በመፍጠርና በመፍጠን በመስራት ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅብናል፡- ርዕሰ መስተዳደር አሻድሊ ሀሰን

ረቡዕ ኅዳር 03, 2018 158

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በየደረጃው ከሚገኙ የክልሉ መንግሥት አመራሮች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው፡፡
የክልሉን የመልማት አቅም፣ እስካሁን በተሰሩ ሥራዎች የተገኙ ስኬቶችንና ተስፋዎች እንዲሁም በቀጣይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሊሰሩ የሚገባቸውን ቁልፍ ተግባራት የተመለከተ የውይይት ሰነድ ርዕሰ መስተዳድሩ አቅርበዋል፡፡
በዚህም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ የልማት ዘርፎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ተፈጥሯዊ አቅም መኖሩን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸው፤ እስካሁን ድረስ በተከናወኑ ጅምር ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ክልሉ ካለው እምቅ ተፈጥሯዊ አቅም አንጻር ብዙ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በተለይ ወርቅን ጨምሮ የክልሉ የማዕድን ሀብት ከክልሉ አልፎ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችል በመግለጽ፤ በየደረጃው ያሉት የክልሉ አመራሮች ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በፍጥነት በጥራትና በአገልጋይነት ስሜት ሊሰሩ እንደሚባ አሳስበዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተሳታፊነትና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በትጋት መስራት ከአመራሩ ይጠበቃል ሲሉ አቶ አሻድሊ ሃሰን ለክልሉ አመራሮች አሳስበዋል፡፡
የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሻሻል፣ የቁጠባ ባህልንና የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ማጠናከር፣ ማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ማጎልበት፣ የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት እንዲሁም የከተማ ልማትና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ሥራዎችን በማጠናከር የህዝቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
በጀማል አህመድ