Search

በሕገ ወጥ የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት በኩል የሚላክ ገንዘብ በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ከማስመሰል ድርጊት ጋር በተያያዘ ሊወረስ ይችላል፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

እሑድ ሐምሌ 27, 2017 269

በውጭ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ከሕገ ወጥ የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቆሙ እና አስተማማኝ እና ሕጋዊ ተቋማትን ብቻ እንዲገለገሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ።

ባንኩ ባስተላለፈው የጥንቃቄ መልዕክት፥ መቀመጫቸውን በአሜሪካን ሀገር አድርገው የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት መካከል በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ የማስመሰል እና ሕገ ወጥ ተግባራትን ፋይናንስ በማድረግ ተግባር የተሳተፉ እንዳሉ ደርሼባቸዋለሁ ብሏል።

እነዚህም ሸገይ ገንዘብ አስተላላፊ፣ አዱሊስ ገንዘብ አስተላላፊ፣ ራማዳ ፔይ (ካሕ) እና ታጅ ገንዘብ አስተላላፊ መሆናቸውን ዘርዝሮ፤ ዓላማቸውም የኢትዮጵያን የፋይናንስ ስርዓት ታማኝነት ሆን ብለው ለመሸርሸር እና የገበያ ዋጋን ለማዛባት መሆኑን አክሏል።

አግባብነት ያላቸው የሕግ አስፈጻሚ አካላት በተቋማቱ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያከናውኑ ጥያቄ ማቅረቡን ጠቅሶ፤ ምርመራውን ተከትሎ በቀጣይ እንደ አስፈላጊነቱ ተገቢ እርምጃዎችን የሚወስድ መሆኑን ገልጿል።

በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት የሚላክ ገንዘብ በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ከማስመሰል ድርጊት ጋር በተያያዘ ምክንያት ሊወረስ የሚችል መሆኑን ባንኩ ጠቁሟል።

በዚህ አግባብ የተላከ ገንዘብ ለታለመለት ተቀባይ የሚደርስ ስለመሆኑ ዋስትና አለመኖሩን ጠቅሶ፤ የዳያስፖራው ማህበረሰብ በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት ገንዘብ ከማስተላለፍ እንዲታቀብ አሳስቧል።

ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ገንዘብ የማስተላለፍ ግብይቶች መከናወን ያለባቸው በመደበኛ እና ቁጥጥር በሚደረግበት የፋይናንስ ሥርዓት አማካኝነት ብቻ መሆኑን ገልፆ፤ በገበያው ውስጥ እንዲሰሩ የተፈቀደላቸውን የሁሉንም ተቋማት የተሟላ ዝርዝር ቀጥሎ በተመለከተው ሊንክ አያይዟል፦ https://nbe.gov.et/mta/