በ6ኛው የፓርላማ ዘመን በተለያዩ ከተሞች የተከበሩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓላት በየጊዜው በርካታ ለውጦች የታየባቸው እንደነበሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ።
አፈ-ጉባዔው በተለይ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዓላቱ በድምቀት እና በእውነተኛ ፌዴራሊዝም ላይ ተመስርተው መከበራቸውን ጠቁመው፤ ክልሎች ያለማንም ጣልቃ ገብነት ራሳቸውን በማስተዳደር እንዲሁም ክልሎች ያላቸውን እምቅ ሀብት በማወቅና በማልማት በዓላቱን በድምቀት ማክበራቸው ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
የዘንድሮውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን የሚያዘጋጀው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ይህንን ክብረ በዓል በድምቀት ለማክበር እያደረጋቸው ያሉ ዝግጅቶችን አፈ-ጉባዔው ከልዑካቸው ጋር ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም በርካታ የልማት እንቅስቃሴዎችን መመልከታቸውን አብራርተው፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፌዴራል ሥርዓቱ የፈጠረለትን ራስን በራስ የማስተዳደር ዕድልን ተጠቅሞ አሁን ላይ ይበል የሚያሰኙ በርካታ የልማት እንቅስቃሴዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ቀደም ብሎ የሕዝቦች የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ፣ ክልሎች በነፃነት ራስን በራስ የማስተዳደር እና በፌዴራል ሥርዓቱ እኩል የመወከል ጥያቄዎች እንደነበሯቸው ያስረዱት አፈ-ጉባዔው፣ እነዚህ ጥያቄዎች ተደምረው ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣ ምክንያት መሆናቸውንም ገልፀዋል።
የለውጡ መንግሥት ከመጣ በኋላ በጥናት ላይ ተመስርቶ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ማድረጉን አስገንዝበው፤ የተለያዩ የክልል ጥያቄዎችም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካኝነት በሰላማዊ መንገድ ምላሽ ማግኘታቸውን አስረድተዋል።
በሀይማኖት ከበደ