በአማራ ክልል ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ተቋማት ተቀናጅተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ብርሃኑ ጎሽም ገለጹ፡፡
በሰው መነገድ እና ሰውን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ታሳቢ ያደረገ የምክክር መድረክ በባሕርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የምክክር መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ብርሃኑ ጎሽም፤ በክልሉ ብሎም በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከልና ለመቆጣጠር የባለድርሻ አካላት ሚና ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለውን በሰው መነገድ፣ ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ለሥራ ወደ ውጭ ሀገራት በሕገ ወጥ መንገድ መላክን ለመከላከል ተቋማት ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ለዚህም የክልሉ መንግሥት የክልላዊ የፍልሰት ማሥተባበሪያ ምክር ቤት፣ የትብብር ጥምረት ጽሕፈት ቤት ማቋቋሚያ ማደራጃ እና የአሠራር መወሰኛ አሰራርን በማፅደቅ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን የሚከላከል አዋጅ ወጥቶ በሥራ ላይ መዋሉንም ጠቁመዋል።
በቀጣይም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀው፤ ባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።
በራሄል ፍሬው