Search

ቤት ሠርተን እናስረክባለን ብለው ሕዝብን በሚያጭበረብሩት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡- ፍትሕ ሚኒስቴር

ሓሙስ ታኅሣሥ 23, 2018 158

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 7ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ በምክር ቤቱ የአሠራር እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ አንቀፅ 92 መሠረት የፍትሕ ሚኒስትሯ ሃና አርዓያሥላሴ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በአገልገሎት አሰጣጥ እና ተደራሽነት እንዲሁም በሕዝብ ስም የሚፈጸሙ የተለያዩ ወንጀሎችን በመመከላከል፣ ጥፋተኞችን በሕግ ተጠያቂ ከማድረግ አንጻር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሠራቸው ባሉት ጉዳዮች ላይ ለሚኒስትሯ ጥያቄ ቀርቧል።
ከሪል እስቴት አልሚዎች ጋር የተያያዙ ማጭበርበሮችን ከመቆጣጠር፣ ለዲጂታል ምህዳሩ የሕግ ማዕቀፎችን ተግባራዊ ከማድረግ እና የተቋሙን ተደራሽነት ከማስፋት አንፃር እየተሠሩ ባሉት ሥራዎች ላይም ጥያቄዎች ቀርበዋል።
ሚኒስትሯ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በየደረጃው አስፈላጊው የሪፎርም ሥራዎች መተግበራቸውን አንስተው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊ የለውጥ ሥራዎችን በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የዜጎችን ዲሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን በተመለከተ ማንኛውም አካል የመብት ጥያቄ ሲኖረው ሕገ መንግሥቱን እና የሀገሪቷን ሕጎችን ባከበረ መንገድ ሊቀርብ ይገባል ብለዋል።
ከሕግ ውጭ የሆኑ ጉዳዮች ሲኖሩ ግን በየደረጃው ተጠያቂነት እንደሚኖርም ነው ሚኒስትሯ ያብራሩት።
የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተም የወንጀል ጉዳዮች በባሕሪያቸው ውስብሰብነት ያላቸው እና ዝርዝር መረጃ እና ማጣራትን የሚፈልጉ በመሆናቸው ጊዜ ሊወስዱ የሚችሉ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
ቤት ሠርተን እናስረክባለን በማለት ማኅበረሰቡን በሚያጭበረብሩ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሰላም ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ሰብዓዊ መብት ጥሰትን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አዳጋች በመሆኑ በምክክር ኮሚሽን እና በሽግግር ፍትሕ በዘላቂነት ሰላምን ለማስፈን እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በፍሬሕይወት ረታ