Search

በ127 ሰዎች ላይ ከባድ የማታለል ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ሰኞ ታኅሣሥ 20, 2018 865

“የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎችን እናስመጣለን” በሚል በ127 ሰዎች ላይ ከባድ የማታለል ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።

ከመዲናዋ መዘመን ጋር ተያይዞ ቀልጣፋና ተደራሽ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖራት መንግሥትና ባለሀብቶች በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ መሆኑ ይታወቃል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ዜጎች ካላቸው ላይ ቆጥበው የነገ ሕይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ በትራንስፖርት ዘርፉ ለመሰማራት የተለያዩ አማራጮችን ይፈልጋሉ።

ተጠርጣሪዎቹ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአነስተኛ ቅድመ ክፍያ የመኪና ባለቤት እናደርጋለን በማለት ከ127 ሰዎች ላይ ከ130 እስከ 350 ሺህ ብር ተቀብለዋል።

የሄሎ ታክሲ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ዮሐንስ፣ ወይዘሪት እንግዳ የሺጥላ እና ሌሎች "መኪና አስመጪ ነን" ባዮችና ተባባሪዎቻቸው በፈፀሙት ከባድ የማታለል ወንጀል ክትትል ሲደረግባቸው እንደነበር ፖሊስ ጠቅሷል።

ግለሰቦቹ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ዜጎችን በማደራጀት በትንሽ ክፍያ የመኪና ባለቤት እናደርጋችኋላን በሚል ባልተገባ መንገድ የበርካቶችን ህይወት አደጋ ላይ ጥለዋል ብሏል።

በአቋራጭ ለመክበር በማሰብ ከድሀው ዜጋ ገንዘብ በመሰብሰብ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚሹ ግለሰቦችም ይሁኑ ተቋማት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

መሰል የማታለል ድርጊት ውስጥ በሚገቡ ላይም ተገቢውን ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስጠንቅቋል።

#EBC #ebcdotstream #AddisAbabaPolice

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: