Search

ታሪካዊ የሆነውን የሀገራዊ ምክክር ዕድል ልዩነቶችን በመግባባት ለመፍታት መጠቀም ይገባል - ዑስታዝ አቡበክር አሕመድ

ዓርብ ታኅሣሥ 17, 2018 151

ታሪካዊ የሆነውን የሀገራዊ ምክክር ዕድል ልዩነቶችን በመግባባት ለመፍታት መጠቀም እንደሚገባ ዕውቁ የእስልምና ሃይማኖት መምህር ዑስታዝ አቡበክር አሕመድ ገለጹ።

ዑስታዝ አቡበክር ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ሲንከባለሉ የቆዩ የልዩነት ትርክቶችን ለማረቅ፣ የጋራችን የሆነች ኢትዮጵያን የወል የአብሮነት እሴቶች ማጎልበት እንደሚገባ አንስተዋል።

ለዚህም መወያየት እና መመካከርን እንደ ሁነኛ አማራጭ አስቀምጠዋል።

ከዚህ አኳያ ሀገራዊ ምክክር መጀመሩ ለአሁኑ ትውልድ ታሪካዊ ዕድል መሆኑን ጠቅሰው፤ በምክክሩ በመሳተፍ ለስኬታማነቱ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሚዲያ በቅጡ ካልተመራ የማህበረሰባዊ መስተጋብር፣ የአብሮነት እና የሰላም መሠረት የሆኑ እሴቶችን የሚያናጋ በመሆኑ መስመር ማበጀት እንደሚያሻ ጠቁመዋል።

እንደ ቻይና ያሉ መንግሥታት ሀገራዊ እሴቶችን የሚንዱ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ከመቆጣጠር ባሻገር በራሳቸው ቅኝት እንዲመሩ ማድረጋቸውን በማውሳት፤ መንግሥት በዚህ ረገድ ያለውን ወሳኝ ሚና አመላክተዋል።

በማህበራዊ ሚዲያ የሚስተዋሉ አሉታዊ መልኮች ከየትኛውም ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ያፈነገጡ መሆናቸውን በማንሳት፣ የእምነት ተቋማት እና ልሂቃን በግል እና በጋራ በትውልድ ግንባታ ላይ አበክረው እንዲሠሩ መክረዋል።

ሀገር የጋራ ነው ያሉት ዑስታዝ አቡበክር፤ የሀገርን መሠረት እና መገለጫዎቿን የሚጻረሩ አካሄዶችን የማረም እንዲሁም ትውልድን የመቅረጽ፣ የማነጽ እና የመገሰጽ ኃላፊነት የሁላችንም ነው ሲሉ ገልጸዋል።

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #NationalDialogue