Search

የተሻሻለ የቡና ዝርያ በማልማት ተጠቃሚ ሆነናል - የሸካ ዞን አርሶ አደሮች

ዓርብ ኅዳር 05, 2018 141

የተሻሻለ የቡና ዝርያ በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሸካ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል በሰጣቸው የቡና ምርጥ ዘር በአንድ ዓመት ውስጥ አመርቂ ምርት ማግኘት እንደቻሉ አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።

ከማዕከሉ የተሰጣቸውን ምክረ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ መቻላቸው ለምርታማነቱ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ነው የገለጹት።

እያለሙት የሚገኘው የቡና ዘር በሽታን የመቋቋም አቅሙ የላቀ እና በምርታማነትም ቢሆን ከበፊቱ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ጭማሪ መሆኑን አብራርተዋል።

በሔክታር 32 ኩንታል ለውጪ ገበያ የሚቀርብ የታጠበ የቡና ምርት ማግኘት የቻሉት አርሶ አደሮቹ፣ ተሞክሯቸውን ለሌሎች ለማስፋት አሁን ላይ ዘር የማዘጋጀት ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በአካባቢያቸው ለሚገኙ አርሶ አደሮች ችግኞችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥ ዝርያውን የማላመድ እና የማስፋት ኃላፊነት እየተወጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል የቡና ተመራማሪ ዋቁማ መርጋ በበኩላቸው፣ የአካባቢውን ሥነ-ምኅዳር ያማከለ፣ ምርታማነቱም በጥናት የተረጋገጠ የቡና ዝርያ የማስተዋወቅ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ያረጁ የቡና ዝርያዎችን በአዲስ በመተካት አርሶ አደሩ የተሻለ ምርት እንዲያገኝ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል ያሉት ደግሞ፣ የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ደረጀ ቱሉ (ዶ/ር) ናቸው።

ከዚሁ ተግባር ጎን ለጎን አርሶ አደሩ የአሠራር ዜዴዎቹን በማዘምመን ምርታማነቱን በእጥፍ እንዲያሳድግ ማዕከሉ በተግባር የተደገፈ ክትትል እና እገዛ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በየዓመቱ በአማካይ ከ240 ሺህ ቶን በላይ ቡና የሚመረት ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ከ54 ሺህ ቶን በላይ የሚሆነው ለዓለም ገበያ ይቀርባል።

በሰለሞን ባረና

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Coffee #agriculture