ኢትዮጵያ ዛሬ ከዘመናት የእርሻ ማሳዎች ትጋትና ከታረሰ መሬት ጠረን ተሻግራ፣ የኢንዱስትሪ ማሽኖች በሚያስተጋቡት የብልጽግና ዜማ የታጀበ የታላቅ ሽግግር ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። ይህ ጉዞ ተራ የኢኮኖሚ ለውጥ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የኢትዮጵያዊነት የጥረትና የጽናት ታሪክ ዳግም የምታድስበት፣ የኢኮኖሚ ነፃነታችንን በገዛ እጃችን የምናጸናበት እና "ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል ብሄራዊ ወኔ የነገውን ብሩህ ተስፋ የምንቀይስበት የታሪክ አውድማ ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሀገራችን የማምረቻ ዘርፍ በወረርሽኝ ስጋት፣ በጦርነት አውሎ ነፋስ ቢናወጥም፣ በመንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ የጥገና እርምጃዎችና በህዝባዊ ንቅናቄው ጥንካሬ ዛሬ ዘርፉ ወደ አዲስ የዕድገት ምህዋር ተመልሷል።
ዝገውና ስራ አቁመው የነበሩ ከ830 በላይ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ዳግም የህይወት እስትንፋስ ዘርተው ወደ ስራ መመለሳቸው የዚህ ትንሳኤ ቁልፍ ማሳያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ( ዶ/ር) መሆናተዉን ተናግረዋል። ከእነዚህም ጎን ለጎን በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ግዙፍ ፋብሪካዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የኢኮኖሚውን ደም ስር እያደሱት ይገኛሉ። ይህ መዋቅራዊ ሽግግር ግብርና ቀስ በቀስ ስፍራውን ለኢንዱስትሪ መሪነት እየለቀቀ መሆኑን የሚያበስር ሲሆን የዘርፉ የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻም ከ30 በመቶ በላይ መሻገሩ የዚህ እውነት ህያው ምስክር ነዉ ።

"የራሳችንን ለራሳችን" የሚለው መርህ ከቃል ባለፈ በተግባር ተተርጉሞ፣ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገቢ ምርትን በአገር ውስጥ መተካት ተችሏል። በተለይም በጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን አልባሳትና በቢራ ብቅል ምርት ላይ የተመዘገበው መቶ በመቶ ስኬት፣ ኢትዮጵያ ራሷን ለመቻል የሰነቀችው ህልም ወደ ምድር መውረዱን ያመላክታል። በማዕድን ዘርፉም ቢሆን የወርቅና የድንጋይ ከሰል ምርትን በማሳደግ፣ ሀገሪቱ ለዘመናት የቆየባትን የጥሬ ዕቃ አቅራቢነት ታሪክ በመቀየር እሴት ወደሚጨምር ምርታማነት እያሸጋገራት ይገኛል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችንም ከሼድ ግንባታ ባለፈ ወደ "ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናነት" በመሸጋገር ላይ ናቸው። እነዚህ ቀጣናዎች ለሀገር በቀል ባለሀብቶች የፈጠሩት ዕድልና ለወጣቶች የከፈቱት የስራ በር፣ የሀገር ውስጥ አቅምን የማነቃቃት ተስፋችንን አብስረዋል። በፓርኮች ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች መካከል 60 በመቶው የሀገር ውስጥ መሆናቸው፣ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን የምታረጋግጠው በልጆቿ ክንድ መሆኑን ዳግም አረጋግጧል።
የሚገርመው ደግሞ ኢትዮጵያ የነገውን ዓለም ቀድማ ለመቀበል ያሳየችው ድፍረት ነው፤ የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን በማገድ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አብዮት መግባቷና ዘመናዊው "የጥራት መንደር" መገንባቱ ምርቶቻችን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና የክብር ቦታ እንዲኖራቸው ያደርጋል። ይህ ሁሉ ጥረት ሀገሪቱን ወደ አምስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት (Industry 5.0) እያሻገራት ሲሆን ይህም የሰው ልጅና የማሰብ ችሎታ ያላቸው ማሽኖች ተቀናጅተው የሚሰሩበት፣ ምርታማነትና የአካባቢ ጥበቃ የሚመጣጠንበት ዘመናዊ ሂደት ነው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ጉዞ ከፋብሪካ ግንባታ ባለፈ የሀገር ክብርን የመመለስ ታላቅ ተጋድሎ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ከትራንስፎርመር እስከ አውቶሞቲቭ ፋብሪኬሽን ያሉ ውስብስብ ቴክኖሎጂዎችን በገዛ ልጆቿ እጅ ማምረት መጀመሯ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የጀመረችው ጉዞ ወደማይመለስበት የከፍታ ምዕራፍ መሸጋገሩን ያረጋግጣል። ይህ ራሷን የምትመግብ፣ የምታለብስና ለዓለም የምትተርፍ ታላቅ ሀገር የመገንባት የታሪክ ድርሳን ነው። ኢትዮጵያ ነገን የምታየው በራስ የመተማመን አይንና በብረት በጠነከረ ክንድ ነው።
#የኢንዱስትሪአብዮት #ኢትዮጵያታምርት #EthiopiaTamirt #ManufacturingEthiopia #EconomicSovereignty #Industry5_0 #Ethiopia