የሐዋሳ ከተማን የውበት፣ የቱሪዝም እና የባህል መዳረሻነት ታሪክ በመቀየር፤ አሁን ላይ የአፍሪካ ግዙፉ የሶላር ሴል ማምረቻ ማዕከል ወደ መሆን መሸጋገሯ፣ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ እያደረገች ያለውን ጥልቅ መዋቅራዊ ለውጥ በጉልህ ያመላክታል።
ይህ የለውጥ ጉዞ የገጠሙ ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚዎች ከመቀየር የጀመረ እና የሀገራችንን የኢኮኖሚ አቅጣጫ ዳግም የቃኘ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሶላር ሴል ማምረቻ ፋብሪካዎችን በመረቁበት ወቅት ያስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የጀመረችውን ትክክለኛ እና ተስፋ ሰጪ ሀገራዊ ጉዞ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
ፈተናን ወደ ዕድል መቀየር እና የገበያ ስብጥር
የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ቀደም ሲል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በጨርቃጨርቅ ምርት ላይ የተንጠለጠለ ነበር። የአጎዋ (AGOA) ዕድል ሲቋረጥ 90 በመቶ የሚሆኑት የፓርኩ ማምረቻ ሼዶች ሥራ አቁመው ባዶ መቅረታቸው፣ የሀገራችን ኤክስፖርት በአንድ ዘርፍ እና ገበያ ላይ ብቻ መመስረቱ ያለውን ከፍተኛ አደጋ አሳይቷል።
መንግሥት ከዚህ አሳሳቢ ክስተት በመማር ግዙፍ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ባደረገው ስኬታማ ጥረት፣ ፓርኩን ወደ ተሻለ እና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ማሸጋገር ችሏል። ይህም አሁን ላይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘርፍ ለታየው ጠንካራ መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን፣ በ2018 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ 45 አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ አስችሏል።
የውጭ ምንዛሬ ግኝት እና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር
በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ይገኝ ከነበረው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ይልቅ አሁን ወደ ሥራ የገቡት የሶላር ማምረቻ ፋብሪካዎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛሉ። ከፋብሪካዎቹ ብቻ በቀጣይ ዓመት ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚገኝ ይጠበቃል። ይህም ከጨርቃጨርቁ ምርት ከ4 እስከ 5 እጥፍ እንደሚበልጥ በንጽጽር ማየት ይቻላል። የዚህ ዓይነቱ ግዙፍ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ በማክሮ ኢኮኖሚው መዋቅር ላይ የኢንዱስትሪ ዘርፉን የመሪነት ሚና ይበልጥ እያጎላው ይገኛል።
በዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ እንደተመላከተው፤ የኢንዱስትሪ ዘርፉ የ13.2 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ከሌሎች ዘርፎች ቀዳሚ ሆኗል። በዚህም ምክንያት በሀገራችን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ላይ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ድርሻውን በ3 በመቶ ማሳደግ የቻለ ሲሆን፣ የግብርናው ድርሻ ደግሞ በ3.6 በመቶ ቀንሷል።
ይህ አኃዝ ግብርናው ላይ በዋናነት የተንጠለጠለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ወደ ትክክለኛው የኢንዱስትሪ መስመር እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የአምራች ኢንዱስትሪው የማምረት አቅም በ4 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ ለጠቅላላ የኤክስፖርት ገቢ 45 በመቶ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
የቴክኖሎጂ ሽግግር፡ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና አውቶሜሽን
በሐዋሳ የተመረቁት የሶላር ሴል ማምረቻዎች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው። የሰውን ጉልበት ብቻ ከመጠቀም ወጥቶ፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና በሮቦቲክስ የታገዘ ፈጣን እና ጥራቱን የጠበቀ አመራረት መጀመሩ በዘርፉ የታየ ትልቅ እመርታ ነው።
ይህ ተግባራዊ እርምጃ መንግሥት አሁን ላይ በስፋት እየተገበረው ካለው "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ እና የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ሥልጠና ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው። የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውህደት፣ በቀጣይ ኮምፒውተሮችን እና ስማርት ስልኮችን በሀገር ውስጥ ለመገጣጠም እና ለማምረት ለተያዘው ሀገራዊ ዕቅድ ጠንካራ መሰረት ጥሏል።
የታዳሽ ኃይል ራዕይ እና የኢነርጂ አቅም
ኢትዮጵያ ካላት የፀሐይ ብርሃን ጸጋ እና እንደ ሊቲየም (Lithium) ካሉ ማዕድናት አንጻር፣ የሶላር ሴል ማምረቱ ያለው ሀገራዊ ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው። በሐዋሳ እስከ 15.3 ጊጋ ዋት፣ በደብረ ብርሃን እና አዲስ አበባ ያሉትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ከ20.3 ጊጋ ዋት በላይ የሶላር ኃይል ማመንጫዎችን የማምረት አቅም ይኖራታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው እንደጠቀሱት ይህ አኃዝ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ 5 ጊጋ ዋት የማመንጨት አቅም ጋር ሲነጻጸር አራት እጥፍ ነው። ይህ ግዙፍ አቅም ሀገራችን ከያዘችው "አረንጓዴ እና ስሉጥ መሠረተ ልማት" እንዲሁም አረንጓዴ ኢነርጂን በስፋት የማመንጨት ስትራቴጂያዊ ግቦች ጋር እጅግ የተጣጣመ ነው።
የሀገር ውስጥ አቅምን ማጎልበት እና የኢንዱስትሪ ትስስር
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እንዳነሱት፣ የሶላር ፓነሎችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥሬ እቃዎችን በስፋት ማቅረብ ያስፈልጋል። ለዚህም የባትሪ እና ሌሎች ተያያዥ ማዕድናት ምርምርና ልማት ወሳኝ ነው። መንግሥት የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄን ተከትሎ የተለያዩ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ባደረገው ርብርብ፣ የተኪ ምርት ድርሻ ወደ 58 በመቶ ከፍ ብሏል።
በተጓዳኝም በተለያዩ ምክንያቶች ምርት አቁመው የነበሩ 993 ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መመለሳቸው፣ የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ትስስርን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።
የሐዋሳው የሶላር ማምረቻ ፋብሪካዎች ምረቃ ኢትዮጵያ ከተረጅነት እና ከውጭ ምርት ጥገኝነት ተላቅቃ፣ በቴክኖሎጂ ወደ ላቀ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ወዳለው የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ እያደረገች ላለው ስኬታማ ሽግግር ህያው ማሳያ ነው።
ሰላምን ማረጋገጥ፣ የሥራ ባህልን ማዳበር እና ምቹ የከተማ ኮሪደሮችን ማስፋፋት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን (FDI) ለማሳደግ እና የዚህን የለውጥ ጉዞ ሞተር ለማፋጠን ቁልፍ ሚና እንዳላቸው መረጃዎች ያረጋግጣሉ።
በለሚ ታደሰ