የሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከላካቸው ምርቶች፤ ከ45.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቱን የልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ማቲዎስ አሸናፊ ግልጸዋል።
የውጭ ባለሀብቶችም ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ውሎችን እየፈጸሙ መሆናቸውን አቶ ማቲዎስ ለኢቢሲ ኤፍኤም አዲስ 97.1 ተናግረዋል።
ኢኮኖሚ ዞኑ ከዚህ ቀደም ጨርቃ ጨርቅ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ እንደነበር የጠቀሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ወደ ልዩ ዞኑ ለመግባት ስምምነት መፈረማቸውን አውስተዋል።
በተለይም የምሥራቅ እስያ ኩባንያዎች ወደ ልዩ ዞኑ ለመግባት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውንም ነው ያነሱት።
በኢኮኖሚ ዞኑ ተሰማርተው ወደ ምርት ሂደት ከገቡት ኩባንያዎች መካከል እንደ ቶዮ ሶላር፣ ካናዳ ሶላር እና ኦሪጂን ሶላር ያሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እንደሚገኙባቸውም ገልጸዋል።
በልዩ ዞኑ ከምርት ባሻገር የሀገር ውስጥ ሠራተኞችን በከፍተኛ ቴክኖሎጂ በማሰልጠን እና በማብቃት፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር ጭምር እየተካሄደ መሆኑን አቶ ማቲዎስ ተናግረዋል።
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ብዝኃ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት እና ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ነው።
በኢኮኖሚ ዘርፍ በተደረገው ሪፎርም በአሠራር፣ ደንብ እና መመሪያዎች ላይ መሰረታዊ ማሻሻያዎች መደረጋቸው እና የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን በመፍታት ለዓለም አቀፍ አልሚዎች አስቻይ የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲፈጠር መደረጉን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል።
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ካሏቸው 177 ሼዶች ውስጥ 150ዎቹ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ባለሀብቶች መያዛቸው ተጠቁሟል።
እየጨመረ በመጣው የኢንቨስትመንት ፍላጎትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ80 በላይ አዳዲስ ኢንቨስትመንት ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ማስገባት ተችሏልም ነው የተባለው።
በለሚ ታደሰ