Search

ውጤታማ የፊስካል ሽግግር በክልሎች መካከል ተመጣጣኝ ልማት ያመጣል፡- አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

ሰኞ ኅዳር 08, 2018 111

ውጤታማና እና ፍትሃዊ የፊስካል ሽግግር ማድረግ በክልሎች መካከል ተመጣጣኝ ልማት ያመጣል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
ከሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ከፌደራል ተቋማት ለተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎች እና ለባለድርሻ አካላት በበይነ-መንግሥታት የፊሲካል ግንኙነቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ማጠናቀቂያ መድረክ መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ ፊስካል ፌደራሊዝም ለፌደራል እና ለክልል መንግሥታት የተሰጡትን ኃላፊነቶች መሰረት በማድረግ የገቢ ምንጮች የሚደለደሉበት እና ወጪን የመሸፈን ኃላፊነት የሚከፋፈልበት መርህ ሲሆን፣ ውጤታማ የፊስካል ሽግግር ለፌደራል ሥርዓቱ ጤናማነት ወሳኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሥልጠናው ዓላማ የክልሎችና የፌደራል ባለድርሻ አካላትበኢትዮጵያ የፊሲካል ፌደራሊዝም ሥርዓት፣ በጋራ ገቢ ክፍፍል፣ በጥቅል ድጎማ በጀት እና በውስን ዓላማ ድጎማዎች ላይ ሕገመንግሥታዊ እና ሕጋዊ መሠረት፣ አሰራሮች፣ መርሆዎች እና ተግዳሮቶች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ከፌደራል መንግሥት በሚደረጉ የፊስካል ዝውውር እና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ውጤታማ አፈጻጸም እንዲኖር ለማስቻል መሆኑን አፈ ጉባኤው ገልጸዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ፌደራል መንግሥት ለክልሎች የሚያከፋፍላቸውን ድጎማም ሆነ የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ሥርዓት ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው በማድረግ የገቢ ክፍፍል ሥርዓቱም ሆነ የድጎማ በጀት ክፍፍሉ በጊዜ ሂደት የሚመጡ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችንና ተግዳሮቶችን እንዲቋቋም፣ ዘመን ተሻጋሪ እና የተረጋጋ እንዲሆን አዋጆችንና ደንቦችን በማውጣት ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
አያይዘውም በተሻሻለው የአሰራር ሥርዓት ምክንያት ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት የክልል መንግሥታት ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን መናገራቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።