የሕግ ታራሚዎች የውኃ፣ የምግብ፣ የመጠለያ እና የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲቀረፉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
የምክር ቤቱ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ማዕከል ገላን፣ አቃቂ ቃሊቲ እና ቂሊንጦ የሕግ ታራሚዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
በምልከታው ማጠቃለያም ክፍተቶችን በማረም ጥንካሬዎችን ማስቀጠል እንደሚገባ ለሚመለከታቸው አካላት አቅጣጫ አስቀምጧል።
በምክር ቤቱ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ በዚሁ ወቅት፥ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የፍተሻ ሥርዓቱን ማሻሻል እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች እና ጠያቂ ቤተሰቦችን እንግልት መቀነስ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
አካል ጉዳተኛ የሕግ ታራሚዎችን ታሳቢ ያደረገ ምቹ የመመገቢያ እና የማደሪያ ቦታ ማመቻቸት እንዲሁም የአዕምሮ ታማሚ የሆኑ ታራሚዎችን የሕክምና መረጃቸውን መሠረት በማድረግ ለአዕምሮ ሕሙማን ማዕከላት ማስረከብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሕግ ታራሚዎችን በማነፅ በሥነ ልቦና አዘጋጅቶ አምራች ዜጋ ሆነው እንዲወጡ ለማስቻል የምክር አገልግሎት መስጠት እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ማከናወን እንደሚገባም ነው ወ/ሮ እፀገነት ያሳሰቡት።
የሕግ ታራሚዎች እና አመራሩ ተቀራርበው በመሥራት በማረሚያ ቤቶች የሚነሱ ቅሬታዎችን በፍጥነት አጣርቶ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ህፃናት ለያዙ ሴት የሕግ ታራሚዎች ማረሚያ ቤቱ ደረጃውን የጠበቀ ንፁህ እና ምቹ መኝታ ቤት በማዘጋጀቱ የቋሚ ኮሚቴው አባላት እውቅና መስጠታቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል የኑስ ሙሉ በበኩላቸው፥ የቋሚ ኮሚቴው ዕይታ ለኮሚሽኑ ቀጣይ ሥራ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
#EBCdotstream #Ethiopia #parliament #standingcommittee #prison