የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዘሪሁን ተሾመ ስለ ቀይ ባሕር ስናወራ ወደብ ስለማግኘት ሳይሆን የባሕር በር ማግኘት ወደሚለው ማተኮር አለብን ይላሉ።
በኢቢሲ የሀገር ጉዳይ መሰናዶ ላይ የቀረቡት አቶ ዘሪሁን ተሾመ፤ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አካባቢ ያላት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከደኅንነቷ እና ከህልውናዋ ጋር የተያያዘ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ደኅንነቷን ለመጠበቅ ከባሕር መራቅ የለባትም ብቻ ሳይሆን የሚገባትን ድርሻ ማግኘት እንዳለባትም አንስተዋል።

በአካባቢው ያለውን ማኅበረሰብ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ ታሪካዊ ዳራውን እና ወቅታዊ የዓለም አቀፍ ሁኔታን ማየት ከተቻለ ኢትዮጵያ ከንግድ ወደብ በላይ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት የሚያስገድዱ ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከባሕሩ በራቀች ቁጥር ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ የሚሄዱ ዘላቂ የደኅንነት አደጋዎች እንደሚኖሩም አቶ ዘሪሁን አስረድተዋል።
የባሕር በር ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው የሚባለው ወደ ባሕር በቀረቡ ቁጥር በአካባቢው የሚነሱ ችግሮችን የመከላከል አቅም የሚጨምር እና የሚመጣውን የደኅንነት አደጋ በአጭሩ ለመቅጨት ስለሚያስችል ነው ሲሉ ገልፀዋል።
በመሆኑም አብሮ ማደግን እና የቀጣናውን ሰላም የሚሻ ሁሉ ለኢትዮጵያ ፍትሐዊ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት እንዳለበት አመላክተው፤ የኢትዮጵያን ፍላጎት የጦርነት ነጋሪት መጎሰም አድርገው የሚወስዱ ወገኖች ካሉ ግን ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል ብለዋል።
በለሚ ታደሰ