Search

ዓባይ ባንክ ለ3 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የ6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

ሓሙስ ኅዳር 11, 2018 109

በ823 ባለ አክሲዮኖች ተመስርቶ በ125.8 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ከ15 ዓመታት በፊት ሥራውን የጀመረው ዓባይ ባንክ አሁን ላይ የተከፈለ ካፒታሉን ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ አድርሷል።

በመላው ሀገሪቱ ከ500 በላይ ቅርንጫፎችን ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ባንኩ ጠቅላላ ሀብቱ 95 ቢሊዮን ብር፣ ካፒታሉ ደግሞ መጠባበቂያን ጨምሮ ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ገልጿል።

ከሐምሌ 07/2017 ዓ.ም ጀምሮ 15ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅት ሲያከብር የቆየው ዓባይ ባንክ የክብረ በዓሉን የማጠናቀቂያ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩም የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አብዱ ሁሴን እና የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ሰለሞን ደስታን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የዓባይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የኋላ ገሠሠ፥ ባንኩ ለደንበኞቹ የላቀ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ባንኩ፤ በተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎቶችም በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።

ባንኩ ይህንኑ ሰናይ ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠል በዛሬው ዕለትም ለ3 የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የ6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

ድጋፉ የተደረገላቸው የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ፣ ነህምያ ኦቲዝም ማዕከል እንዲሁም ዝግባ የሕፃናትና የአረጋውያን መርጃ ድርጅት እያንዳንዳቸው የ2 ሚሊዮን ብር ከባንኩ ተረክበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ሰለሞን ደስታ፥ የሀገሪቱ የባንክ ዘርፍ በመንግሥት የፖሊሲ ድጋፍ አትራፊ ሆኖ መዝለቁን አንስተው፤ መጪው ጊዜ ግን የውድድር ስለሚሆን በቴክኖሎጂ እና በአሰራር ልቆ ለመገኘት በትጋት መሥራት ይገባል ብለዋል።

በኤዶም አማረ

#ebcdotstream #abaybank #15thanniversary #communityservice