ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የተመለከቱ ጉዳዮችን ስታነሳ የተለያዩ የተሳሳቱ ትርክቶች ከየአቅጣጫው ይነሳሉ።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የነበረው ዓለም አቀፍ ጫና ለዚህ አንዱ ማስረጃ ነው።
አሁንም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የወደብ ባለቤትነትን ጥያቄ ስታነሳ የተሳሳቱ ሃሳቦችን የሚያሰራጩ አካላት ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።
የሕዳሴ ግድብ ተሟጋች እና የኪንግስ ኦፍ ዓባይ ሚዲያ መስራች ኡስታዝ ጀማል በሽር ከኢቲቪ አዲስ ቀን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተነሱብንን ብዙ ጩኸቶች በሕዳሴ ግድብ ተወጥተነዋል፤ ይህ ልምድ ደግሞ ለሌሎች ሥራዎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅምን በተመለከተ ለሚነሱ ዓለም አቀፍ ጫናዎች ከወዲሁ አጀንዳዎችን መርጦ የመመከት ሥራ ማከናወን እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡
ልዩነቶችን ወደ ኋላ በመተው ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም እንደሚገባ ጠቁመው፤ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያረጋግጡ ሥራዎችን እውን ለማድረግም የሚዲያው ድርሻ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ እና ሥነ-ጽሑፍ መምህር የሆኑት አቶ ዘመዱ ደምስስ በበኩላቸው፤ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይን ለይቶ አጀንዳን በተደራጀ መንገድ ወደ ማኅበረሰቡ የማስረጽ ሥራ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት፡፡
ከትምህርት ቤት ጀምሮ ብሔራዊ ጥቅም ምን ማለት እንደሆነ እና የሀገርን ዓላማ ለማሳካት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ነው የጠቀሱት፡፡
ትርክት ለአንድ ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ያለው ሚና ላቅ ያለ ስለመሆኑ አንስተው፤ እያንዳንዱ ዜጋ በሚይዘው ተንቀሳቃሽ ስልክ አማካኝነት ሀገራዊ ጥቅምን ማጉላት እንደሚችልም ነው የገለጹት፡፡
ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም ዘብ የሚቆም ጠንካራ ትውልድ በመፍጠር ረገድም ሚዲያዎች ትልቅ ሚና እንዳላቸው አመላክተዋል።
በሜሮን ንብረት