Search

ከመብረቅ አደጋ ራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንችላለን?

በአብዛኛውን ጊዜ የዝናብ ወቅትን ተከትሎ በተለይም በክረምት ወራት የመብረቅ አደጋ ሲከሰት ይስተዋላል፡፡
ለመሆኑ መብረቅ ምንድነው? እንዴትስ ይፈጠራል? አደጋና ከአደጋው ማምለጫ መንገዱስ?
ለነዚህ ጥያቄዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር ታደሰ ተረፈ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአትሞስፌሪክና ኦሺየኒክ ሳይንስ መምህር የነበሩና የዘርፉ ተመራማሪ ምላሽ አላቸው፡፡
በዳመና ውስጥ ተጭነው በሚንቀሳቀሱ ኔጋቲቭ እና ፖዘቲቭ ቻርጆች መካከል በሚፈጠር ግጭት ምክንያት መብረቅ እንደሚከሰት ይታመናል።
እንቅስቃሴያቸው ኃይል ስለሚፈጥር አየሩን በከፍተኛ ደረጃ ያሞቀዋል፡፡ የመብረቅ ሙቀት እስከ 30 ሺህ ዲግሪ ሴልሺየስ ሊደርስ ይችላል፡፡
በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ድምጽና ብልጭታ ይፈጠራል፡፡ ብልጭታውን ቀድመን አይተን ዘግየት ብሎ ድምጹ ይሰማል፡፡
ታዲያ ኤሌክትሮኖች ወደ ደመናው እና ወደ ምድር ሲጓዙ ከአካባቢው ከፍ ያለ ኤሌክትሪክ አስተላላፊ መሆን የሚችልን እንደ ተራራ፣ዛፍ፣ ከአካባቢው ከፍ ያለ ህንጻ፣ ባዶ ሜዳ ላይ ከፍ ብሎ የተገኘ ሰውም ቢሆን ሲያገኙ እሱን እንደአስተላላፊ ይጠቀሙበታል፡፡
አደጋው የሚከሰተው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ አንድ ሰው ወይም ሌላ ነገር በመብረቅ ተመታ የሚባለው ከፍተኛ ሙቀት ያለው የኤሌክትሪክ ሞገድ በሰውነቱ ሲገባ ነው፡፡
በመብረቅ መመታት ለሞት የሚያበቃ ትልቅ አደጋ ነው፡፡እንደ ዘርፉ ባለሙያዎች ገለጻ መብረቅ ዝናቡ ከሚጥልበት እስከ አስር ማይል ርቀት ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡
ለመሆኑ ከመብረቅ አደጋ ራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንችላለን?
በዝናብ ወቅት የቤት በርና መስኮትን መዝጋት፣ ከከፍታ ቦታ መራቅ፣ በመኪና ውስጥ ከሆኑ ዘጋግቶ መቀመጥ፣ ሜዳ ላይ ለብቻ አለመገኘት ከመብረቅ አደጋ ራስን ለመጠበቅ ያስችላል፡፡
መብረቅ ወደ የኤክትሪክ ገመድ ገብቶ ተጨማሪ የኤሌክተሪክ ፍሰት በመጨመር ኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ሊያቃጥል ይችላል፡፡ ስለዚህ ሬጉሌተር መግጠም ወይም በመብረቅ ሰዓት ሶኬቶችን መንቀል እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
ህንጻዎች እንዳይመቱ አናታቸው ላይ የብረት ገመድ ተዘርግቶ አንዱን ጫፍ ወደመሬት በመቅበር መከላከል እንደሚቻል ባለሙያው ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡
በድንገት አንድ ሰው በመብረቅ ቢመታ በፍጥነት ራቁቱን መሬት ላይ ማስተኛት ወይም አንገቱ ሲቀር መሬት ውስጥ መቅበር ሳይንሳዊ መድህን መሆኑን ይነገራል፡፡ በተጨማሪም የጤና ባለሙያ ክትትል ያስፈልጋል፡፡
እንደ የአሜሪካ የበረራና የጠፈር አስተዳደር (ናሳ) መረጃ በመብረቅ አደጋ በዓለም ላይ በየዓመቱ በአማካኝ 24 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ፤ እስከ 240 ሺህ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡
በጌታቸው መላኩ