የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምቾት ያላቸውን የፕሪሚየም (አልማዝ) ደረጃ መቀመጫዎችን ለማሠራት ከኮሊንስ ኤሮስፔስ ጋር የግዢ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ግዢው አየር መንገዱ የደንበኞቹን ፍላጎት እና ምቾት ለማሻሻል የሚያደርገው ጥረት አንድ አካል መሆኑን ነው ከአየር መንገዱ የተገኘው መረጃ የሚያመላክተው።
እነዚህ ምቹ የቢዝነስ ክፍል መቀመጫዎች አየር መንገዱ በቅርቡ ላዘዛቸው የኤርባስ A350 እና ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች የሚገጠሙ ናቸው።
የኮሊንስ ፕሪሚየም መቀመጫዎች ምቾትን የሚሰጡ፣ ለመስራት፣ ለመዝናናት እና ለመመገብ ሰፊ ቦታ የሚሰጡ መሆናቸውም ነው የተጠቆመው።
ስምምነቱ የአፍሪካ መሪ አየር መንገድ በሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኮሊንስ መካከል ባለው ጠንካራ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ አየር መንገዱ በቅርቡ ያዘዛቸው አውሮፕላኖችን ምቾት ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳው ታውቋል።
ሃምሳ ስድስት 737 ማክስ አውሮፕላኖች በኮሊንስ የአልማዝ የቢዝነስ ክፍል መቀመጫዎች የሚሠሩላቸው ሲሆን፣ ይህም ለአውሮፕላኖቹ ውበት፣ ለረጅም ርቀት መንገደኞቹ ደግሞ ምቾትን ይጨምራል ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ኦፕሬቲንግ ዋና ኦፊሰር ረታ መላኩ አየር መንገዱ ደንበኛን ያማከለ አየር መንገድ እንደመሆኑ መጠን የደንበኞቹን የበረራ ላይ ምቾት የሚጨምር ስምምነት ከኮሊንስ ኤሮስፔስ ጋር በመፈራረሙ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኮሊንስ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑት የአልማዝ ደረጃ መቀመጫዎች ከላቀው የአየር መንገዱ አገልግሎት ጋር በማጣመር የተሳፋሪዎችን የበረራ ላይ ምቾት እና ነጻነት በመጠበቅ ኢትዮጵያዊ መስተንግዶን ከፍ የሚያደርግ እንደሆነም አቶ ረታ ገልጸዋል።
በኮሊንስ ኤሮስፔስ የደንበኞች እና የንግድ ልማት ም/ፕሬዝዳንት ሲንቲያ ሙክሌቪች እንደገለጹት የኮሊንስ ፕሪሚየም የቢዝነስ ደረጃ መቀመጫዎች አየር መንገዱን የሚመጥን ጥራት ያላቸው እና የደንበኞቹን ምቾትን የሚጨምሩ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ስሙ ገናና የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞችን የሚመጥን እና አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉት ደንበኞቹ ዘንድ ተወዳጅነቱ እንዲጨምር የሚረዳ ስምምነት መሆኑንም ተናግረዋል።
ኮሊንስ ኤሮስፔስ፣ የ‘RTX’ ንግድ፣ ለዓለም አቀፍ ኤሮስፔስ እና መከላከያ ኢንዱስትሪ ሲሆን፣ በዘርፉ የተቀናጀ እና ቀልጣፋ አገልግሎትን የሚሰጥ መሪ ኩባንያ ነው።