መንግሥታት በቆይታቸው የሚያሳልፉት ውሳኔ እና የሚፈጽሙት ስምምነት ጠቃሚ ይሁን ጎጂ ለቀጣዩ ትውልድም የሚተላለፍ መሆኑ አይቀርም።
ኢትዮጵያ በኢ-ፍትሃዊ መንገድ የተነጠቀችው የባሕር በር ጉዳይ ግን ከዚህ በተቃራኒው እንዴት አጣነው? ማን ሰጠ? ማን አፀደቀው የሚሉ ሰነዶችን እንኳን ፈልጎ ማግኘት አለመቻሉ ዛሬም እንቆቅልሽ ነው።
ኢትዮጵያ መተንፈሻዋ የሆነውን የባሕር በር አማራጭ ስትነጠቅ መልክዓምድሯ ብቻ ሳይሆን ዜጎቿም ስለጉዳዩ እንዳይተነፍሱ ተደርጎ ነበር፡፡
ተከድኖ የበሰለው ጉዳይ ዛሬ ላይ በጋለ መልኩ ሲወጣ፤ በወቅቱ ለነበረው የሽግግር መንግሥት የሀገርን ይዞታ ቆርጦ ለመስጠት ማን ስልጣን ሰጠው?፣ ስምምነቱ የተደረገባቸው ሕጋዊ ፋይሎችስ የት አሉ? ብሎ ለሚጠይቅ መልስ መስጠት አልተቻለም።
ይባስ ብሎ ደግሞ በሽግግር ሕጉ ቻርተር አንቀፅ 4 ያለውን “የሽግግር መንግሥቱ የሀገርን ጥቅም ያከበሩ ውሳኔዎችን ያሳልፋል“ የሚለው አንቀጽ ስለምን ተጣሰ? እና ሌሎች ጥያቄዎችን ያስነሳ ሆኗል፡፡
ከኢቢሲ የአዲስ ቀን ሀገር ጉዳይ መሰናዶ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕግ ባለሙያው አንዱዓለም በእውቀቱ፣ የሽግግር መንግሥት የሀገርን ግዛት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ አሳልፎ የመስጠት ስልጣን አለው ወይ? የሚለው ሀሳብ ሊፈተሽ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
መንግሥታት መንበረ ስልጣናቸውን ሲረካከቡ የዶክመንት ልውውጥ እንደሚያደርጉ ያነሱት ባለሙያው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሕግ አግባብ በተደገፈ መልኩ ስምምነቱን ያደረገበት ብሎም በተቋሙ ደረጃ የተደገፈ ምንም ዓይነት ሰነድ ያለመኖሩን ገልፀዋል፡፡
ይህም የባሕር በር አማራጭ በቋሚነት አሳልፈን የሰጠንበት ስምምነት እንደሌለ ይደግፋል ያሉት ባለሙያው ዛሬ ላይ ጥያቄው ወደፊት ሲመጣ መነጋገር ተገቢ መሆኑን ነው የሚያነሱት።
በሀገራት መካከል የሚደረጉ ስምምነቶችን ከሕግ አንፃር የሚቃኘው ‘የቬና የስምምነት ሕግ ኮንቬንሽን’ አንቀጽ 46 ሀገሪቱን በማስተዳደር ላይ ያለው መንግሥት ይህን መሰል ውሳኔ የማሳለፍ ስልጣን ከሌለው፤ ቢኖረውም እንኳ ውሳኔው የሀገር ውስጥ መሠረታዊ ሕግን የሚታለለፍ ከሆነ የመጪው መንግሥት ውሳኔውን አልቀበልም የማለት መብቱን እንደሚደነግግ አስረድተዋል፡፡
የህልውና ጉዳይ ህጋዊ ድጋፍ እንዳለው የገለፁት ባለሙያው፤ ኢትዮጵያ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮን በዋቢነት በማጣቀስ ጥያቄዋን የምታስመልስባቸው አስቻይ ሁኔታዎች ስለመኖራቸው አስገንዝበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የባሕር በር አማራጭ እንድታጣ ከስምምነት የተደረሰበትን ሰነድ በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስረዱበት ወቅት ይህን ጉዳይ በተመለከተ ሕጋዊ ማስረጃ ተፈልጎ ማግኘት አለመቻሉን ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡
በአፎሚያ ክበበው