የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እንዲስፋፋና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ባሳዩት ቁርጠኛ አመራር፤ የዓለም አቀፍ ኢስላሚክ ሪቴል ባንኪንግ (IBRA) "የ2025 ምርጥ የባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ" (Best CEO of the Year) ሽልማትን አሸነፉ።
አቶ አቤ ለዚህ ሽልማት የበቁት፤ አገልግሎቱ በአገራችን እንዲጀመር የሕግ ማዕቀፎች እንዲቀረጹ በማድረግ፣ ባንኩ አገልግሎቱን በቀዳሚነት እንዲጀምር በመምራት እንዲሁም ከባንክ አገልግሎት ተገልሎ የነበረውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ያደረገ የፋይናንስ አካታችነት ሥራ በመሥራታቸው እንደሆነ ተገልጿል።

ስትራቴጂያዊ ለውጦችን በማድረግ ሲቢኢ ኑርን መሪ የፋይናንስ ተቋም ማድረጋቸውም ለሽልማቱ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ተብሏል።
በተጨማሪ በ11ኛው የዓለም አቀፍ ኢስላሚክ ሪቴል ባንኪንግ ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ኑር አገልግሎት የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ተብሎ የተሸለመ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ኑር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኑሪ ሁሴን ሽልማቱን ተረክበዋል።
በዘርፉ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተወዳደሩ 80 ሀገራት መካከል ሞሮኮን፣ ናይጄሪያንና ኬንያን የመሳሰሉ ሀገራትን በመብለጥ 27ኛ ደረጃን መያዝ የቻለች ሲሆን፤ ሳዑዲ ዓረብያ፣ ማሌዥያና ኢራን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እ.ኤ.አ የ2022 የዓለም ኢስላሚክ ፋይናንስ ሽልማት በጂቡቲ ሲካሄድ፤ ኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ ላካሄደችው ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎች፤ በተለይ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ለማስፋፋትና አካታችነትን ለማረጋገጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅናና ሽልማት ማግኘታቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ ያካሄደችው ሰፊ ማሻሻያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እያገኘ ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።