Search

በቶተንሀም ደጋፊዎች እንደ ከሀዲ የሚታየው ካምቤል

በእነዚህ ሁለት ክለቦች መካከል ያለው ተቀናቃኝነት ዓለም ላይ ካሉ ደርቢዎች ከቀዳሚዎቹ አንዱ ነው፡፡ አርሰናል ከቶተንሀም ሆትስፐር፡፡
100 ዓመታትን በተሻገረው የእግር ኳስ ታሪካቸው በተገናኙ ቁጥር በተጫዋቾች መካከል ሜዳ ላይ ከሚፈጠረው ትንቅንቅ እስከ ደጋፊዎች ግጭት የደርቢው አንዱ መገለጫ ሆኖ ዓመታትን አሳልፋል፡፡
በሁለቱ ክለቦች ስቴዲየም መካከል ያለው ቅርበት የጎረቤታሞቹ ጨዋታ ይበልጥ ፉክክር የሚታይበት እና ትክክለኛው የሰሜን ለንደን ተወካይ አንዳቸው ብቻ መሆናቸውን ለማሳየት ያገኟቸውን ክብሮች ከመቁጥር የሌላኛውን በድን ውድቀት እስከ መዘርዘር ይደርሳሉ፡፡
ክለቦቹ ካላቸው የተቀናቃኝነት ታሪክ አንጻር በፍጹም አንዳቸው ከአንዳቸው ተጫዋች በቀጥታ ማስፈረም አይፈልጉም፡፡ የአንዳቸውን መለያ የለበሱ ተጫዋቾችም በፍጹም የሌላኛው መለያ መልበስ አይፈልጉም፡፡
ነገር ግን 2001 ላይ ይሄንን ታሪክ የቀየረ አንድ ክስተት ተፈጥሯል፡፡ ሶል ካምቤል በዋናው ቡድን 9 ዓመት ከቆየበት ቶተንሀም ሆትስፐር ወደ አርሰናል የተዛወረበት ፍጹም ያልተጠበቀ ነበር፡፡
ምንም እንኳን በቶተንሀም ቤት ዋንጫ ማግኝት ባይችልም በግሉ ድንቅ ጊዜን ያሳለፈው ሶል ካምቤል በጊዜው ውሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ባርሴሎና እና ኢንተር ሚላንን ጨምሮ በበርካታ የአውሮፓ ክለቦች ቢፈለግም ምርጫውን አርሰናል ማድረጉ የነጭ ለባሾቹን ደጋፊዎች በእጅጉ ያሳዘነ ነው፡፡
ከጃማይካውያን ቤተሰቦች የተወለደው ሶል ካምቤል በወቅቱ “በትልቅ ደረጃ የመጫዎት ፍላጎት ስላለኝ ነው አርሰናልን የተቀላቀልኩት” ማለቱ ደግሞ የቶተንሀም ደጋፊዎችን አሁንም ድረስ የሚያበሳጫቸው ነው፡፡ በትልቅ ደረጃ የሚለው ሃሳቡ ቶተንሀም ከአርሰናል ያነሰ ክለብ እንደሆነ መናገሩ ነው በሚል ለ9 አመት ስሙን ጠርተው እንዳልዘመሩለት አሁን ቁጥር አንድ የሚጠሉት ተጫዋች እሱ ነው፡፡
እንግሊዛዊው ተጫዋች በነጻ ዝውውር ወደ አርሰናል ካመራ በኋላ በመድፈኞቹ መለያ የመጀመርያ ጨዋታውን ከቀድሞ ክለቡ በዋይት ሃርት ሌን ባደረገበት ዕለት የቶተንሀም ደጋፊዎች ሙሉ 90 ደቂቃ ኳሱን ከመመልከት ይልቅ የከዳቸውን ተጫዋች ሲዘልፉ ያመሹበት ሆኖም አልፏል፡፡
ከአርሰን ቬንገር ጋር የመስራት ዕድል ያገኝው ካምቤል እንዳለውም በአርሰናል የ6 ዓመት ቆይታው ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 6 ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡ በተጨማሪም በሰቭን ጎራን ኤሪክሰን በሚሰለጥነው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ቋሚ ተሰላፊ የሆነበትንም ዕድል ፈጥሯል፡፡
ሶል ካምቤል በቶተንሀም ከአካዳሚ ጀምሮ ከ10 አመት በላይ ቢቆይም ሁሉንም ፈተናዎች ችሎ ከአንደኛው የሰሜን ለንደን ክለብ ወደ ሌላኛው የተዛወረ በትለልቅ ደረጃ የሚጠቀስ የመጀመርያው ተጫዋች ነው፡፡
የአርሰናል ደጋፊዎችም ከቶተንሀም ጨዋታ ሲኖራቸው ካምቤል የአለማችንን ምርጡን ክለብ መርጧል በማለት የቶተንሀም ደጋፊዎችን እንደ ማብሸቂያም ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ