Search

ለዜጎች የመፍትሔ አማራጭና ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት የሆኑት የጋራ መኖሪያ ቤቶች

ሰኞ ኅዳር 15, 2018 79

በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው በጀርመን አደባባይ፣ በአየር ጤና እና በግራር አካባቢ የተገነቡ 1 ሺ 287 የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተከናውኖ ተመርቋል።
በዘጠኝ ወራት ጊዜ ተገንብተው የተጠናቀቁት መኖሪያ ቤቶች 24 ሕንፃዎች ሲሆኑ ከ11 እስከ 18 ወለል ያላቸው ናቸው፡፡
 
የመኖሪያ መንደሩ የልጆች መጫወቻ ስፍራዎችን፣ የስፖርት ሜዳን፣ የመዝናኛ ስፍራዎችን፣ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን እና የጋራ መገልገያዎችን ያሟላ ነው፡፡
ከኢቲቪ ዜና ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ የነበራቸው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወ/ጊዮርጊስ በከተማዋ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ለማሻሻል ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አማራጮች መቅረጽ መጀመሩን አንስተዋል፡፡
የግሉን ዘርፍ ወደዚህ ሥራ የማስገባት ጥረት እንዳለ የገለጹት ኃላፊዋ ፤ አምስት አማራጮችን በመከተል ወደሥራ እንደተገባ ነው የተናገሩት።
በጀርመን አደባባይ፣ በአየር ጤና እና በግራር አካባቢ ተገንብተው የተመረቁት የመኖሪያ ቤቶችም በዚህ መንገድ በግል እና በመንግሥት የጋራ ጥረት መገንባታቸውን ገልጸዋል።
እስከአሁንም የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን በመጥቀስ ከ380 ሺ በላይ ቤቶች መገንባት መቻሉን ተናግረዋል።
 
በሜሮን ንብረት