Search

ተገልጋዮችን ከእንግልት እያሳረፈ ያለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት

ሰኞ ኅዳር 15, 2018 79

መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ  ቀልጣፋ በሆነ መንገድ በአጭር ጊዜ እየሰጠ ይገኛል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ እና ታማኝ ለማድረግ በአዲስ አበባ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በቅርቡ በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እየተስፋፋ ይገኛል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባሳለፍነው መስከረም ወር አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

የአገልግሎቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ሻሜቦ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ጊዜ እና ገንዘብ ቆጣቢ በማድረግ እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ 

ማዕከሉ አሁን ላይ በ7 ተቋማት 20 አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ከበደ ሻሜቦ፤ በቀጣይ ሌሎች አገልግሎቶችም እንደሚጨመሩ ተናግረዋል፡፡  

በማዕከሉ እየተሰጠ ባለው አገልግሎት የተገልጋዮችን እርካታ ማረጋገጥ እንደ ተቻለ የጠቆሙት አቶ ከበደ፤ አገልግሎቱ ከተጀመረ እስካሁን 1 ሺህ 948 ተገልጋዮችን ማስተናገድ እንደተቻለ ገልፀዋል፡፡

የተገልጋዮች መረጃ በቴከኖሎጂ የተደገፈ ነው ያሉት አቶ ከበደ፤ አገልግሎቱን ለማስፋት በቀጣይ 60 አገልግሎቶችን በማዕከሉ መሰጠት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

አገልግሎት ሲያገኙ ያገኛናቸው ተገልጋዮች፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ መጀመሩ ትልቅ እረፍት እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

አገልግሎት ለማግኘት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወርን በማስቀረት በአንድ ቦታ ሁሉንም አገልግሎት ማግኘት በመቻላቸው ጊዜአቸውን ሆነ ገንዘባቸውን እንደ ቆጠበላቸውም ተገልጋዮቹ አስታውቀዋል፡፡

በሀይማኖት ከበደ