Search

ኢትዮጵያና ቻይና በዘመናዊ የጉምሩክ አስተዳደር ግንባታ ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

ረቡዕ ኅዳር 17, 2018 50

የኢትዮጵያ እና የቻይና የጉምሩክ ተቋማት በዘመናዊ የጉምሩክ አስተዳደር ግንባታ ላይ በትብብር ለመስራት እና ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የፊርማ ስነ ስርዓቱን የከወኑት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እና የቻይናው ጉምሩክ አስተዳደር ሚኒስትር ዴኤታ ዋንግ ጁን ናቸው።

ስምምነቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሠረተ አሰራር፣ የተቋም አቅም ግንባታ፣ የሰው ኃይል ልማት፣ የእውቀት ልውውጥ እና የቴክኒክ እውቀትን መጋራት ላይ ለመስራት ያለመ ነው ተብሏል።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በዚሁ ወቅት ሙስናን፣ ማጭበርበርን፣ ኮንትሮባንድን እና ሌሎች ሕገ-ወጥ የንግድ ልምዶችን ለመዋጋት በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ስምምነቱ ወደስራ ሲገባ በተለይ ለአምራቾች፣ ለአስመጪና ላኪዎች እንዲሁም ለሌሎች የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የተሻለ እድል የሚያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የቻይናው ጉምሩክ አስተዳደር ሚኒስትር ዴኤታ ዋንግ ጁን በበኩላቸው፤ ሀገራቸው በጉምሩክ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም እና በጉምሩክ መሠረተ ልማት ማሻሻል ላይ ኢትዮጵያን እንደምትደግፍ አስታውቀዋል።

ሁለቱም ሀገራት ለዘመናዊ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ዘመናዊ የጉምሩክ ስርዓት ለመፍጠር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በብሩክታዊት አስራት

#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #China #Customs