ዓለም አቀፉ የኢንተርፕረነርሺፕ ኔትወርክ (GEN) በየጊዜው በሚያወጣው የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት (GEW) ደረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ለኢንተርፕረነርሺፕ አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር በመሥራት ረገድ ለሳምንታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የቀዳሚነቱን ሥፍራ ይዛ መቀጠሏን የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) አስታወቀ።
ውጤቱ የተገኘው ኢንስቲትዩቱ ባስተባበራቸው እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተሳተፉባቸው 9 ሺህ 758 ሁነቶች አማካኝነት መሆኑን በኢንስቲትዩቱ የኢንተርፕረነርሺፕ ሥነ-ምህዳር ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ዱጋሳ ተናግረዋል።
"በጋራ እንገንባ" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት፣ ከ200 በላይ ሀገራት እየተሳተፉ እንደሚገኙ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ በውድድሩ አልጄሪያ እና ብራዚልን አስከትላ ኢትዮጵያ በሰፊ ልዩነት እየመራች መሆኗን ገልጸዋል።
ይህ ውጤት የተገኘው ከኖቬምበር 1 ቀን ጀምሮ ለ1 ወር እየተካሄደ ባለው የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት እና ከዚያ ቀደም ዘርፉ ላይ በተሠራው ሥራ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከማወዳደሪያ ሁነቶቹ መካከል ዘርፉን የተመለከተ የግንዛቤ ሥራ መሥራት፣ ለኢንተርፕረነሮች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የፖሊሲ ሀሳቦችን ማቅረብ እና ኢንተርፕረነሮች የሚገጥሙአቸው ችግሮች የሚፈቱባቸውን መንገዶች ማፈላለግ ይገኙበታል ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የኢንተርፕረነርሺፕ ኔትወርክም (GEN) ኢንተርፕረነርሺፕን ለማነቃቃት የሚሠሩ ተጨባጭ ሥራዎችን ተከታትሎ እየመዘገበ የሀገራትን ወቅታዊ ደረጃ እንደሚያወጣ ነው አቶ ዱጋሳ የጠቆሙት።
ከኖቬምበር 1 ቀን ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት ነገ በዕውቅና ፕሮግራም እንደሚጠናቀቅ ጠቅሰው፣ ሳምንቱ በዘርፉ በርካታ ሥራዎች የተከናወኑበት እንደነበር ገልጸዋል።
ሥልጠናዎች፣ ኢንተርፕረነሮችን ከአጋሮች ጋር ማገናኘት፣ የፖሊሲ ውይይቶች እና ሌሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በሳምንቱ መከናወናቸውንም ዘርዝረዋል።
ሁነቶቹ ኢንተርፕረነሮች ሀሳባቸውን የሚሸጡባቸው መድረኮች ያመቻቹ በመሆኑ፤ በርካቶች ሀሳባቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ መነሳሳትን ፈጥረዋል ነው ያሉት።
ሳምንቱ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በአዲሱ የሥልጠና ፖሊሲያቸው ኢንተርፕረነርሺፕን እንዲያካትቱ ለተቋማቱ አሰልጣኞች እና አመራሮች የአሰልጣኞች ሥልጠና የተሰጠበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በኢንተርፕረነርሺፕ ሳምነቱ የተለያዩ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን አንስተው፣ በውይይቶቹ የተሳተፉ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ወደየመጡበት ሲመለሱ ለዘርፉ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን እንደሚፈቱ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ ውድድር ከ4 ቀናት በኋላ ኖቬምበር 30 እንደሚጠናቀቅ የጠቀሱት አቶ ዱጋሳ፣ ኢትዮጵያ በውድድሩ እንደእስካሁኑ 1ኛ ደረጃን ይዛ ታጠናቅቃለች ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ከኖቬምበር 30 በኋላ ለአሸናፊው ሀገር ዕውቅና እንደሚሰጥ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ 1ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የሚገኘው ዕውቅና እንደ ሀገር ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
"ኢትዮጵያ 1ኛ ሆና ካጠናቀቀች ኦሎምፒክን እንዳሸነፈች ይቆጠራል" ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህም ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ለዘርፉ ድጋፍ ለማግኘት፣ ሀሳብ ያላቸው ሰዎች ሀሳባቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩበት ዕድል ለማመቻቸት እና ሌሎች በርካታ ዕድሎችን የምታገኝበት እንደሆነ ነው የጠቆሙት።
መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን እና ይህም ሀሳብን ወደ ሀብት በመቀየር ለሀገር ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አቶ ዱጋሳ ተናግረዋል።
በለሚ ታደሰ
#ebcdotstream #entrepreneurship #GEN #GEW2025 #Ethiopia