Search

ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው የትብብር ኢኮኖሚ ሞዴል

ዓርብ ኅዳር 19, 2018 15

ኢትዮጵያ አዲስ የኢኮኖሚ እሳቤ ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝ ይታወቃል።
ይህም በፅኑ መሠረት ላይ የቆመ እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋግጥ ያለመ ነው።
ይህን እውን ለማድረግ የሀገር ውስጥ ገቢን የማሳደግ፣ ገቢ ምርትን የመተካት እና ወጪን በራስ አቅም የመሸፈን ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
በዓለም ዙሪያ ተግባራዊ ከሚደረጉት በጥቅሉ ሁለት ዓይነት የኢኮኖሚ ሞዴሎች መካከል አንደኛው ዋነኛው ተዋናይ የግሉ ዘርፍ የሚሆንበት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ መንግሥት ዋነኛ ተዋናይ የሚሆንበት ነው።
የመደመር መንግሥት ከእነዚህ ሞዴሎች አንደኛውን ለብቻው መተግበር ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ የማያደርግ መሆኑን በመገንዘብ፤ የትብብር ኢኮኖሚ ሞዴልን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ይህን በተመለከተ የኢቢሲ አዲስ ቀን የዜና መሰናዶ እንግዳ ጋብዞ አነጋግሯል።
የምጣኔ ሀብት መምህር እና ተመራማሪው መሐመድ ኢሳ (ዶ/ር)፥ የትብብር ኢኮኖሚ ሞዴሉ በተለያዩ ዘርፎች ለተገኙ ለውጦች እና ስኬቶች ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኗን ጠቅሰው፤ በንግዱ ዘርፍ መንግሥት ለአዳዲስ እሳቤዎች አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር በመሥራት ላይ ነው ብለዋል።
የግሉ ዘርፍ ለተጨማሪ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ለሀገር ከፍታ የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከት ይገባዋል ያሉት ባለሙያው፤ የዘርፉ ተዋንያን በየወቅቱ አዳዲስ ስልጠናዎችን በመስጠት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የቢዝነስ አመራር መፍጠር እንዳለባቸው አመላክተዋል።
የቢዝነስ አመራሮች ዘርፈ ብዙ ዕውቀት ማዳበር ከቻሉ እና ዘርፉ በአግባቡ ከተመራ ለሀገራዊ ኢኮኖሚው ዕድገት የላቀ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ