በአማራ ክልል ሕገወጥ የንግድ ሰንሰለትን በመቆጣጠር የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል።
በወቅታዊ የክልሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ መግለጫው የሰጡት የቢሮው ኃላፊ ኢብራሂም ሙሃመድ (ዶ/ር)፤ በክልሉ ሕገወጥ ንግድን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት አራት ወራት 278 ሺህ በሚሆኑ ነጋዴዎች ላይ በተደረገው ድንገተኛ ቁጥጥር እና ፍተሻ፣ 39 ሺህ የሚሆኑት ከቀላል እስከ ከባድ ሕገወጥነት ታይቶባቸው የማስተካከያ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
አያይዘውም ባለፉት አራት ወራት 380 የንግድ ድርጅቶች ምርት ደብቀው በመገኘታቸው አስፈላጊው እርምጃ እንደተወሰደ አንስተዋል።
በተጨማሪም 117 ሺህ ሊትር ነዳጅ ተደብቆ መያዙን ገልፀው፣ በአሁኑ ወቅት በየማደያዎች የሚደረገው የቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው ያመላከቱት።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተገኙ ሕገወጥ ኬላዎችን የማንሳት ሥራ ስለመከናወኑ ጠቅሰው፣ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
በቅርቡ የተደረገውን የመንግሥት ሰራተኞ የደሞዝ ጭማሪን ተከትሎ፣ ያለምክንያት የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የገበያ ማዕከላትን፣ የእሁድ ገበያን እንዲሁም ሌሎች የገበያ ማረጋጊያ መንገዶችን የማስፋት ሥራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
በሳሙኤል ወርቅአየሁ