ደጋፊዎች የክለቦች ሃብት ናቸው፡፡ በትኬትና እና ቁሳቁስ ሽያጭ የክለባቸውን የፋይናንስ ጡንቻ ለማጠንከር ይሰራሉ። ተጫዋቾች አቅማቸውን የበለጠ እንዲጠቀሙ ብርታትና ሀይል ይሆናሉ። የክለቡን መለያ ምልክት (ብራንድ) ያሳድጋሉ፡፡ ማህበረሰባዊ ትስስርን ይፈጥራሉ። የእግር ኳስ ደረጃቸው ያደጉ ሀገራት ደግሞ የቴሌቪዥን ስርጭት ክፍያ በተመልካቾቻቸው ብዛት ታሳቢ በማድረግ የገንዘብ ክፍፍል ይደረግላቸዋል፡፡ እግር ኳስ አብዝቶ በሚወደድባት በኢትዮጵያም ለወትሮው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሀብቱ ደጋፊው ነው ይባል ነበር፡፡
በእርግጥም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሀብቱ ደጋፊው ነው። እሱን የሚመጥን እና ደጋፊዎቹን ወደ ሜዳ የሚስብና ከዚያ እንዳይጠፉ የሚያደርግ ስርዓት ግን ያስፈልገዋል። ባለፉት 7 ዓመታት የኢትዮጵያ ላዕላይ ሊግ ራሱን በራሱ በማስተዳደሩ ክለቦች የበለጠ ተጠቃሚ መሆናቸው የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ሻምፒዮን የሚሆነው ክለብ ከ150 ሺህ ብር ወደ ሚሊዮኖች ተሸጋግሯል፡፡ ሁሉም ክለቦች በየደረጃቸው የድርሻቸውን ያገኛሉ፡፡

ይህ የሆነው ግን ከ2013 ዓመተ ምህረት በፊት በነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተፅእኖ ፈጣሪነት ነው፡፡ ከዚያ በመለስ ባሉ ዓመታት ሊጉ በአስተዳደር ስርዓቱ ቢዘምንም፣ ከቲቪ መብት ወደ ካዝናው የሚያስገበው ዳጎስ ያለ ገንዘብ ቢጨምርም የደጋፊዎች መራቅ ግን ለነገው ጉዞ ስጋትን የሚያጭር ነው፡፡ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንዲመለሱ ስራዎችን መስራት ይኖርበታል፡፡
የሊጉ መርሀ ግብሮች ሲወጡ ደጋፊዎቹን ታሳቢ የሚያደርግ አይደለም በሚል ይወቀሳል፡፡ የትኬት ዋጋ መናር እና በስራ ሰዓት ጨዋታዎች መከናወናቸው ከሜዳ አርቆናል የሚሉም አሉ፡፡ የጨዋታ ሰዓቶች በእኩለ ቀን መደረጋቸው ከደጋፊ ባሻገርም ለተጫዋቾች አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልፁም አልጠፉም፡፡
"ቀትር ነው፣ ከሰማይ ወደ ምድር የሚወረወረው እሳት አይደለም ሩጦ ለመጫወት ጥላ ስር ቁጭ ለማለት እንኳን የሚከብድ ነው፡፡ አሰልጣኛችን በንድፈ ሀሳብም በተግባርም የነገረንን ሜዳ ላይ ለመፈፀም የተለየ ቁርጠኝነት ያስፈልግሃል። እውነት ለመናገር 7 ሰዓት ላይ ከመጫወት ተጠባበቂ ወንበር ላይ መቀመጥ ሳይሻል አይቀርም" ይህንን ንግግር የተናገረው በፕሪሚየር ሊጉ ከ10 ዓመት በላይ የተጫወተ ስመጥር ተጫዋች ነው፡፡

አሰልጣኞችም የቀን መርሀ ግብሮች ፈተና እንደሆነባቸው ይመሰክራሉ፡፡ ለአመጋገብም ለሜዳ ላይ ፍልሚያም የማይመች ይሉታል፡፡ ሊጉ ከዓመታት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ የተደሰቱት ብዙዎች ናቸው፡፡ ያ በአዲስ አበባ ሰማይ ስር ጎልቶ የሚሰማው ህብረ ዝማሬ፣ ያ በአዲስ አበባ ስታድየም ምልክት የሆነው የደጋፊዎች ፈጠራ የሆነው የሞዛይክ ውድድር ሊመለስ ነው ብለው የተደሰቱት ብዙዎች ነበሩ፡፡
የአዲስ አበባ ስታድየም እድሳትን ተከትሎ ብሎም የዲኤስቲቪ ስልታዊ ፎርማት ሊጉ የሚኮራበትን የደጋፊዎቹን ሀብት ያጣ ይመስላል። ከ5 ዓመት በፊት የስታድየም ወንበሮች ጦማቸውን አያድሩም ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ግን ወንበሮች የሰው ያለህ ይላሉ፡፡

ከ5 ዓመት በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስና ቡና ከትኬት ሽያጭ ብቻ በዓመት እያንዳንዳቸው ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ያገኙ ነበር፡፡ የክልል ክለቦችም ምንም እንኳን ደረጃውን የጠበቀ ሜዳ ባይኖራቸውም በሜዳቸው ሲጫወቱ (ከነችግሩም ቢሆን) የሚፈጥሩት ድባብ አሰደሳች ከመሆኑም ባሻገር የአካባቢው ማህበረሰብ ጨዋታውን ተገን በማድረግ ገቢ ያመነጭ ነበር፡፡
በ2018 ዓመተ ምህረት በአዲስ አበባ ስታድየም የተደረጉ ጨዋታዎችን ብንመለከት ሜዳው የሞላው በሸገር ደርቢ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በመለስ ያሉት ጨዋታዎች ወንበሮች ደጋፊዎችን አብዝተው የሚጣሩ ናቸው፡፡ ለወትሮው ቅዱስ ጊዮርጊስም ኢትዮጵያ ቡናም ሲጫወቱ ሜዳው በአብዛኛው ይሞላ ነበር፡፡

ዛሬ ላይ ግን ጥላ ፎቅም በግድ ነው። ይህንን የሊጉ አስተዳዳሪ አካል ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል። ጨዋታዎች የደጋፊን ኪስና የስራ ሰአት ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል የሚሉ አስትያየት ሰጭዎች አሉ፡፡ በየ3 ቀኑ የሚደረጉ ጨዋታዎች በክለቦች ባይወደዱም ቢያንስ ደጋፊ ሜዳ እንዲገኝ የአዲስ አበባ ስታድየም መብራትን ተጠቅሞ መስራትም አዋጭ ነው የሚሉም አሉ፡፡
ከምንም በላይ ግን ጨዋታዎችን ቅዳሜ እና እሁድ ከጧት እስከ ማታ ቢደረግ የሚሉ አሉ። ይህ ግን ሊጉ ያለ አቅሙ ጨዋታዎችን በማብዛቱ ክረምቱ ሳይገባ ለመጨረስ የሚደረገውን ትግል የሚረብሽ ነው፡፡ ሆነም ቀረም ፕሪማየር ሊጉ በደጋፊዎች ታጅቦ እንዲደረግ ፍላጎታቸውን ታሳቢ ያደረገ መርሀግብርን ይሻል፡፡
ሀብታሙ ካሴ