በዓለም አትሌቲክስ የነሐስ ደረጃ የተሰጠው የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ የአንድ ቀን የአትሌቲክስ ውድድር ነገ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ይደረጋል።
ዓለም አቀፍ አትሌቶች ጭምር የሚሳተፉበትን ይህን ውድድር በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ተሰጥቷል።
የዓለም አትሌቲክስ የውድድር ዳይሬክተር ፒርስ ኦካላጋን ይህ አጋጣሚ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ አዲስ መንገድ የሚከፍት ነው ብለዋል።
ዓለም የኢትዮጵያን አትሌቶች በሚገባ ያውቃቸዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ መጠቀም ለቀጣዩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትልቅ መሠረት የሚጥል እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህ በተወሳሰበ ዓለም ውስጥ የአፍሪካ አትሌቶች በሌላው ዓለም ለመወዳደር የቪዛ ፈተና እንደሆነባቸው የገለጹት ፒርስ ኦካላጋን የኮንቲኔንታል ቱር ውድድር በአዲስ አበባ መደረጉ ብዙ ነገር አቃሎላቸዋል ብለዋል።
ከሥድስት ሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ ስመጣ የአዲስ አበባ ስታዲየም ትራክ አልነበረውም፤ በዚህ ፍጥነት ትራኩ ተሰርቶ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መዘጋጀቱ ተዓምር ነው ብለዋል።
ለአትሌቲክሱ የተሰጠው ትኩረት በዚሁ መቀጠል እንዳለበት የተናገሩት የውድድር ዳይሬክተሩ የኮንቲኔንታል ቱሩ በቦትስዋና፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ከመካሄዱ በፊት በኢትዮጵያ መጀመሩም ታሪካዊ ነው ብለዋል።