በስዊዘርላንድ ሉዛን በተካሄደው 88ኛው የዓለም አቀፉ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር (AIPS) ጉባኤ ላይ በተሰጠ ድምፅ ኢትዮጵያ የ2027ቱን ታላቅ መድረክ እንድታስተናግድ በሙሉ ድምፅ መመረጧን የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በይፋ አስታውቋል።
ይህ ታሪካዊ ስኬት የሀገሪቱን ስም በዓለም አቀፍ ስፖርት መድረክ ዳግም ከፍ የሚያደርግ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ከ300 በላይ አንጋፋና ስመ ጥር የዓለም ስፖርት ጋዜጠኞች ወደ ሯጮቹ ምድር አዲስ አበባ የሚመጡበትን ዕድል አመቻችቷል።
በጉባኤው ላይ የሚሳተፉት ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸውና በታላላቅ የሚዲያ ተቋማት ውስጥ የስፖርቱን ዓለም የታሪክ ማህደር የፃፉ ናቸው።
ከእነዚህም መካከል የአበበ ቢቂላን በባዶ እግር የመሮጥ ገድል እስከ ኃይሌ ገብረ ሥላሴና ቀነኒሳ በቀለ የድል ታሪኮች ለዓለም ያስተዋወቁ አንጋፋ ጋዜጠኞች ይገኙበታል። እንዲሁም የማራዶናን ታሪካዊ ግቦች በወጣትነታቸው የዘገቡና አሁን ደግሞ እንደ ላሚን ያማል ያሉ ወጣት ከዋክብትን ቃለ-መጠይቅ ያደረጉ አንጋፋ የስፖርት መጽሐፍት ደራሲያንና ጋዜጠኞች የኢትዮጵያን እንግዳ ተቀባይነት ለማየት ወደ መዲናዋ ይተማሉ።
ከሚዲያ ባለሙያዎቹ በተጨማሪ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የፊፋ እና የካፍ ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የሌሎች ዓለም አቀፍ ስፖርት ተቋማት መሪዎች በዚሁ መድረክ ላይ እንደሚታደሙ ይጠበቃል።
ይህንን ታላቅ ዝግጅት ማስተናገድ ለኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ስፖርት ዕድገት ትልቅ ትርጉም አለው።
በተለይም ለወጣት ጋዜጠኞች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠር ባሻገር ከዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመመሥረት ልምድ እንዲቀስሙ ሰፊ በር ይከፍታል።
በተጨማሪም ጉባኤው ማህበሩን በኢኮኖሚ የሚያጠናክሩ አጋጣሚዎችን ይዞ የሚመጣ ሲሆን ኢትዮጵያ ለታላላቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ያላትን ዝግጁነትና የስፖርት አምባሳደርነቷን ለዓለም ማህበረሰብ ዳግም የምታሳይበት ወርቃማ ዕድል እንደሚሆን ማህበሩ አክሎ ገልጿል።