Search

ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በሙሉ አቅማቸው እንደሚደግፉ የገለጹት የዱባይና አካባቢው ኢትዮጵያውያን

እሑድ ኅዳር 28, 2018 52

በዱባይና ሰሜን ኢምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመደመር መንግሥት የጀመራቸው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሀገራችንን ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያሸጋግሩ በመሆናቸው በሙሉ አቅማን እንደግፋቸዋለን ሲሉ ተናገሩ።

ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ይህን ያሉት 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንን ትናንት በዱባይ ባከበሩበት ወቅት ነው።

በተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚህም፥ መንግሥት ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ እየገነባቸው የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን ከተስፋ ብርሃን ወደ ተጨባጭ ስኬት የሚያሸጋግሩ ናቸው ብለዋል።

አምባሳደር ጀማል፥ የመደመር መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው እውነተኛ ፌዴራሊዝም ሕዝባችንን ይበልጥ በማቀራረቡ፣ የሕዳሴ ግድብን በድል ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይ የታቀዱ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ፣ የነዳጅ ማጣሪያ እና የቤት ልማት ፕሮጀክቶችም በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የጋራ ርብርብ እንደሚሳኩ ያላቸውን ሙሉ እምነት ገልጸዋል።

መላው ኢትዮጵያውያን በሕገ መንግሥቱ የተጎናጸፉትን መብት በማስጠበቅ፣ ከፋፋይ ትርክቶችን በመመከት ለዘላቂ ሰላምና ልማት ደጀን እንዲሆኑ አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ የተሳተፉት የዱባይና አካባቢው የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ አባላት በኮሚኒቲ አመራሮቻቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዳያስፖራው የብሔረሰቦች ቀንን ሲያከብር የብሔር፣ የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነቶችን እንደ ጌጥ በመጠቀም ኢትዮጵያዊነቱን በማጉላት እንዲሁም ለለውጥ የገባውን ቃል በማደስ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

#ebcdotstream #Ethiopia #nationalitiesday #Diaspora #UAE #Dubai