የሰኔ አጋማሽ የአዲስ አበባ ብርድ እና ካፊያ ሲጀምር፣ በአቧሬ አካባቢ በሚገኝ አነስተኛ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት እማሆይ ስጋት ከእርጅናቸው በላይ ይጫናቸው ነበር።
አንዲት የተባረከች ቀን ግን ያንን የሰቀቀን ኑሮ እስከ ወዲያኛው የምታስረሳቸው ሆና ተከሰተች።
ያልታሰቡ ክቡር እንግዳ ጎራ ብለው፣ ከዚያ የብርድ እና የጎርፍ ጭንቀት ሊገላግሏቸው መወሰናቸውን አበሰሯቸው።
እማሆይም እንግዳቸውን "ልጄ ክፉ አይንካህ" ብለው መርቀው ስጦታቸውን ተቀበሉ፤ ከዚያ ወዲያም ከክረምቱ ሰቀቀን ተገላገሉ።
ያ በ2011 ዓ.ም ከአዋሬ የእማሆይ ደሳሳ ጎጆ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተሰማው የተስፋ ድምፅ አቧሬን አስውቦ ብቻ አልቀረም።
የተስፋ ብሥራቱ ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ በይፋ ለተጀመረው ትልቅ ሀገራዊ ንቅናቄ መሠረት በመሆን የበርካታ አቅመ ደካሞችን ሕይወት ቀይሯል።
በዚሁ መንፈስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 ዓ.ም. የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በይፋ አስጀምረዋል።
ይህ ሀገራዊ ንቅናቄ ልክ እንደ አዋሬ እማሆይ ሁሉ፣ በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ የብዙ አቅመ ደካሞችን የኑሮ ቀዳዳ ለመድፈንና የተስፋ ብርሃን ለመፈንጠቅ ያለመ ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን ይበልጥ በማጠናከር፣ ዘንድሮም በትልቅ ዝግጅት ወደ ሥራ የገባው ይህ የክረምት በጎ አድራጎት ንቅናቄ በአሁኑ ወቅት በአረንጓዴ አሻራ፣ በቤቶች እድሳት እና በማዕድ ማጋራት ተግባራት በሰፊው ቀጥሏል።
የክረምት ዝናብ ለኢትዮጵያውያን የቸርነትና የበረከት ምልክት በመሆኑ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሰፊ በር ከፍቷል።
ከአዋሬ እማሆይ ቤት የተነሳው የደስታ ፈገግታ፣ ዘንድሮም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ለመቀየር በቁርጠኝነት መቀጠሉ የዚሁ ሀገራዊ ንቅናቄ ህያው ምስክር ነው።
በሃና ምንዳሁን