Search

ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ማጠንጠኛ የሆነው ዕሳቤ

እሑድ ኅዳር 28, 2018 49

 
የመደመር እሳቤ ያለፈውን ጠቃሚ ታሪክ ከነገው ተስፋ ጋር በማሰናሰል፣ ኅብረብሔራዊት ኢትዮጵያን በቁሳዊና በሰብዓዊ ክብር ወደ ላቀ የብልፅግና ከፍታ የሚያሸጋግር የጋራ መንገድ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም መግለጻቸው አይዘነጋም።
ይህ ጉዞ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ፣ ኢትዮጵያን ለሌሎችም ተምሳሌት እንድትሆን የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍን የጀመረ ነው።
የመደመር መንግሥት ዋና ትኩረትም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ናቸው።
የመደመር ጽንሰ-ሀሳብ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ፣ ምርታማነት እንዲያድግ እና የተገልጋዮች እርካታ እንዲጨምር በተሠሩ የሪፎርም ሥራዎች ውጤት ማስመዝገቡንም ተናግረዋል።
የመደመር መንግሥት ፈጠራንና ፍጥነትን የድህነት መውጫ ቁልፍ አድርጎ እየሠራ መሆኑን ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።
በመንግሥት ተቋማት ያሉ ክፍተቶችን መነሻ በማድረግ መፍትሔዎችን ጭምር ያመላከተ በመሆኑ፣ የዘርፉን የአሠራር ሥርዓት በምክንያታዊነት ለመፈተሽና በግብዓትነት ለመጠቀም እድል መፍጠሩንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም በመንግሥት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎችን ለአብነት ያነሱት ሰብሳቢው፤ በተለይም እንደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ያሉ አዳዲስ አሠራሮችን፣ የአገልግሎት ጥራትን፣ ፍጥነትን እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
 
በቢታኒያ ሲሳይ