Search

ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ይፋ አደረገ

ማክሰኞ ኅዳር 30, 2018 384

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ይፋ አድርጓል።
በዚሁ መሠረት የምርጫ ድምፅ የሚሰጥበት ቀን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሆነ የጊዜ ሠሌዳው አመላክቷል።
ቦርዱ እስካሁን ስለሠራቸው የቅድመ-ምርጫ ሥራዎች በተመለከተ እና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በ2018 ዓ.ም ለሚያከናውነው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተለያዩ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
በቦርዱ የፀደቀ የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ይፋ የተደረገ ሲሆን በዚህም መሠረት የዕጩዎች ምዝገባ ከጥር 1 እስከ የካቲት 1/2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
የምረጡኝ ቅስቀሳ /የምርጫ ዘመቻ/ ከጥር 1 እስከ ግንቦት 19/2018 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፣ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 7 እስከ መጋቢት 7/2018 ዓ.ም እንደሚከናወን በጊዜ ሠሌዳው ተመላክቷል።
ሆኖም የመራጮች ምዝገባን ራስን በራስ መመዝገብ ከጥር 15 ጀምሮ እስከ መጋቢት 7 ማድረግ እንሚቻል ተገልጿል።
የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የድምፅ መስጫ ቀን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚሆን ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ይፋዊ የምርጫ ውጤት መግለጫ ቀን ሰኔ 4/2018 ዓ.ም መሆኑን ቦርዱ ይፋ አድርጓል።
በሞላ ዓለማየሁ