Search

የሀገራዊ ምክክሩ ቀጣይ ወሳኝ ምዕራፎች

ረቡዕ ታኅሣሥ 01, 2018 42

ሀገራዊ ምክክር በዜጎች መካከል ያሉ መሠረታዊ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት፣ ዘላቂ ሰላም እና ብሔራዊ መግባባት የሰፈነባት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ሁሉንም አሳታፊ በሆነ መንገድ የጀመረውን ሂደት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ ወደ ኋላ የሚቀር ክልል እና የከተማ አስተዳደር እንደማይኖር እና በኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ አካታች የምክክር ሂደት ወሳኝ መሆኑን አስታውቋል።
ከዚህ አኳያ በትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራን ለማካሄድ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ለኢቢሲ ገልጸዋል።
በመጪዎቹ ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ዋና የምክክሩን ጉባዔ ለማካሄድ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተው፤ በጉባዔው ዜጎች በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት በመምከር ወደ ጋራ መግባባት ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በተለያዩ ክልሎች የተካሄደው የአጀንዳ ልየታና የተወካዮች መረጣ ሂደት በትግራይ ክልልም እንደሚከናወን አመላክተዋል።
በሌላ በኩል 4 ሺ የሚደርሱ የሕዝብ ተወካዮች የሚሳተፉበትን ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ማካሄድ የኮሚሽኑ ቀጣይ የቤት ሥራ ስለመሆኑም አንስተዋል።