Search

በሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደት የተፈጠሩ ቁርሾዎችን እንደ መልካም ዕድል የተጠቀሙ ሀገራት

ረቡዕ ታኅሣሥ 01, 2018 111

የሀገራት ምሥረታ ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንዱ የተለያዩ እና ራሳቸውን የቻሉ ግዛቶችን በኃይል ወይም በማግባባት መጠቅለል እና አንድ ሀገር መፍጠር ነው፡፡

ሁለተኛው በውስጥ የሚፈጠሩ ፍትጊያዎችን በማቻቻል የሁሉንም ፍላጎት ያካተተ ሀገር መገንባት ነው፡፡ በመጀመሪያው ሂደት ሀገረ መንግሥታቸውን የመሰረቱ በርካታ ሀገራት ውድመትን ያስከተሉ ግጭቶች ተከስቶባቸዋል፡፡

በሂደቶቹም የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ አብዮቶች እና አመጾች ነበሩ፡፡ ውስጣዊ አመጾችም ቢሆኑ በርካታ ቁርሾዎችን ጥለው ማለፋቸው አይቀርም።

በዚህ ሂደት ያለፉ በርካታ ሀገራት በጉልበትም ይሁን በስምምነት ተዋሕደው እንደ ሀገር ጉዞ ከጀመሩ በኋላ ግን ችግሮቻቸው እንዳይደገሙ አድርገው ፈትተዋቸዋል፡፡ ልዩነት ፈጥረው ያጋጯቸውን ጉዳዮችን በመግባባት እና በሕግ ፈትተዋል፡፡

ያጋጩአቸው ጉዳዮች ላይ ተነጋግረው የሁሉንም ጥያቄ የሚመልስ ሥርዓት ፈጥረው እንደ ሀገር ቀጥለዋል፡፡ ከፈተናዎቻቸው ተምረውም አንድነታቸውን በማጠናከር ጠንካራ ኢኮኖሚ እስከመገንባት ደርሰዋል፡፡

እንደዚህ ውጤታማ የሆኑ ሀገራት ውጤታማነታቸው ምስጢር ግን በውስጥ ጉዳያቸው ሌላ አካል አለማስገባታቸው ነው፡፡ በተቃራኒው በውስጥ ቅሬታ አሳብበው ሁለተኛ ወገን ያስተናገዱ ሀገራት ከነበሩበት ከፍታ ወርደው እንደ ሀገር ለመቀጠል እንኳን ፈተና ውስጥ ገብተዋል፡፡

እንደ ሶሪያ፣ የመን፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ሌሎች በርካታ ሀገራት ለውስጣቸው ግጭት ሌላ ወገን በመጋበዛቸው እንደሀገር ፈተና ውስጥ የገቡ ናቸው፡፡

ዛሬ ዓለምን የምትመራው ታላቋ አሜሪካ ወደ ዛሬዋ ጥንካሬዋ ያመራት እ.አ.አ. ከ1861 እስከ 1865 የቆየችበት የእርስበርስ ጦርነት ነው፡፡ አሜሪካውያን በሰሜን እና ደቡብ ተከፍለው ባሳለፉት የአምስት ዓመታቱ ጦርነት የትኛውንም ቡድን አሸናፊ እንዳላደረገ የተረዱት ብዙ ውድመት ከደረሰ በኋላ ነበር፡፡

ጦርነቱ የሰሜኑን ክፍል በመሩት አብረሃም ሊንከን አሸናፊነት ቢጠናቀቅም ያንን ከፍተኛ ውድመት ያደረሰው እከሌ ነው በማለት የጦስ ፍየልን ከመፈለግ ቁጭ ብለው ወደ መወያየት ገብተው ነበር ችግሮቻቸውን የፈቱት፡፡ የግጭቱ መነሻ የሆነውን ባሪያ አሳዳሪነትን በሕግ ሽረው፣ ኅብረታቸውን በማጽናት ጠንካራ ሀገር መሥርተዋል፡፡

ያላግባባቸውን እና ለዚያ የከፋ እልቂት ያደረሳቸውን ጉዳይ ምን እንደሆነ በመለየት ተናግረውበት የሚያግባባቸውን የቃልኪዳን ሰነድ አዘጋጁ፡፡ ከዚያ ኪሳራ በመነሳት የመሰረቱት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታቸው ዛሬ ሁሉንም የሚገዛ፣ ሁሉም አሜሪካውያን የሚያስማማ የቃልኪዳን ሰነዳቸው ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በዚህ ሂደትም በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ተፅዕኖ ሥር ሊወድቁ የማይችሉ ተቋማትን ፈጥረዋል፡፡

ለጥፋቱ መስጠት ያለባቸውን እርምት ከሰጡ በኋላ ወደኋላ ተመልሰው እሱን እያሰቡ ሲነታረኩ አልኖሩም፡፡ ይልቁንስ አሜሪካ እንኳን ለተወለደባት ቀርቶ ከየትኛውም የዓለም ክፍል ሄዶ የመኖር ዕድል ላገኙ ሰዎች ሁሉ የምትመች ሀገር አድርገዋታል፡፡

ሌላዋ በሀገረ መንግሥት ምሥረታ ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ያለፈችው ዛሬ የዓለማችን ጠንካራ ኢንዱስትሪ መሪ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ጀርመን ነች፡፡

ጀርመን በፐርሺያ ወታደራዊ ኃይል እና ኦቶቫን ቢስማርክ በሚመሩት ኃይል መካከል የተደረገው ጦርነት በ1871 በኦቶቫን ቢስማርክ ኃይል አሸናፊነት ተጠናቅቆ ነው የዛሬዋን ጀርመንን የመሠረተው፡፡

39 ራሳቸውን የቻሉ ግዛቶችን በማዋሃድ የጀርመን ፌዴራላዊ መንግሥትን የመሠረተው ሂደት ግን አልጋ በአልጋ የነበረ ሳይሆን በበርካታ ኪሳራ ውስጥ ታልፎ ነበር፡፡

ችግሮቹ የተፈቱት ኦቶቮን ቢስማርክ በመሩት እውነተኛ እና አካታች የፖለቲካ ሪፎርም ነበር። ይህ ሪፎርም ወደ ሁለት ቡድኖች ተከፋፍለው የነበሩት 39ኙ ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦችን ያካተተ ፍትሃዊ የፖለቲካ ሥርዓትን በመፍጠር ታላቋን ጀርመን መሥርቷል፡፡

ያ እርሾም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ወደ ምሥራቅ እና ምዕራብ ተከፍላ በግንብ የተለያየችውን ጀርመን መልሶ አንድ ያደረገ ነበር፡፡

ፈረንሳይ ለአንድ ምዕተ ዓመት ያህል (1789 እስከ 1870ዎቹ) በፍፁም ንጉሳዊ አገዛዝ፣ በሕገ መንግሥታዊ ንጉሣዊ አገዛዝ፣ በሪፐብሊክ እና በንጉሠ ነገሥት ሥርዓቶች ውስጥ አልፋለች።

እነዚህ መቶ ዓመታት በውስጣዊ መናወጥ ያሳለፈችው የፈተና ጊዜ ነበር፡፡ በሦስተኛው ሪፐብሊክ (1870-1940) ውስጣዊ ቀውሷን በመፍታት ወደ መረጋጋት መምጣት የጀመረችበት ቢሆንም፣ ውስጣዊ አለመረጋጋቱ ግን ቀጥሎ ነበር።

ንጉሣዊው ሥርዓት በሪፐብሊክ በተተካበት በዚህ ጊዜ የሪፐብሊኩ መሪዎች አካታች ሥርዓትን ጽንፈኝነትን ከሚከላከል ጠንካራ ሕግ ጋር በማዋሃድ ፈረንሳይን ሊያረጋጉ ችለዋል፡፡

በሂደትም ማኅበረሰቡን በማንቃት ፈረንሳይ ወደ ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንድትመጣ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ ሕዝቡ ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞችን በድምጹ እንዲቀጣ ማድረግ ተችሏል፡፡ ለዚህ ሁሉ ቁልፉ ጉዳይ ደግሞ ጠንካራ የዴሞክራሲ እና ሕዝባዊ ተቋማት መፈጠራቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ

ኢትዮጵያ በጥንታዊ ሀገረ መንግሥት ታሪኳ በርካታ ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎችን ስታስተናግድ ኖራለች፡፡ ረጅም ታሪክ ያለው ሀገረ መንግሥት ያላት ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎችን ስታስተናግድ ኖራለች፡፡

ከነገሥታት ዘመን እስከ ሶሻሊዝም፣ ከሶሻሊዝም እስከ አሁን ባለው የሀገረ መንግሥት ጉዞ በርካታ ቁርሾ የፈጠሩ መንገዶች ታልፈዋል፡፡ በተለይም ከ1950ዎቹ የጀመረው አዲስ የዘመናዊ ፖለቲካ ንቅናቄ እና ንቅናቄውን ለማስወገድ የተደረጉ ጉዞዎች በርካቶችን ሰለባ አድርጓል፡፡

ያ ሂደት ደግሞ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የመጣችበትን የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ጥያቄ ውስጥ እስከ ማስገባት ደርሶ ነበር፡፡

ባህላችን፣ ወጋችን እና ታሪካችን በሥርዓቱ በኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ አልተካተተም የሚሉ በርካታ ቡድኖች ወደ ከ1950ዎቹ ጀምረው ትጥቅ ትግል የገቡ ሲሆን፣ ያ ሂደት ዛሬም ፍጻሜውን ያለገኘ ነው፡፡

እንቅስቃሴው ኢትዮጵያን ወደ አደገኛ ገደል እየገፏት በነበረበት ወቅት ነበር የ2010 ዓ.ም ለውጥ የመጣው፡፡ ለውጡን ያመጣው የመደመር መንግሥት የቀድሞ ስብራቶችን አርሞ ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን ለመገንባት እየሠራ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደሚገልጹት የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ገና አልተጠናቀቀም፡፡

በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው ገጽ 287 ላይ፣ የፖለቲካ መረጋጋትና መግባባት በሀገር ደረጃ መፍጠር የሚቻለው የፖለቲካ ሥልጣን ለሰፊው ማኅበረሰብ ለጋራ ጥቅም እንደሚውል ሲታመን እና መልካም አስተዳደር ሲሰፍን እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

"ብዝኃ ማንነት ያለው ማኅበረሰብ ፍላጎቶች በታሪክ ሂደት የመጣጣም ዕድል ካላገኙ፣ ሰብአዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉድለቶችን ፈጥረው፣ የፖለቲካ መግባባትና መረጋጋትን ያወሳስቡታል" የሚለው የመደመር መንግሥት ሀሳብ ኢትዮጵያ ያለፈችበትን ሁኔታ የሚያመላክት ነው።

"ብዝኃ ማንነት ባለበት ሀገር ዴሞክራሲ፣ ፖለቲካዊ መረጋጋት እና መግባባትን የሚያስገኘው የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መቻቻል እና መተሳሰብን የሚያስቀድሙ ከሆነ፣ እንዲሁም በወንድማማችነት መርሕ የሚመሩ ከሆነ ነው፡፡

በመሆኑም ብዝኃነት ባለበት ሀገር፣ መንግሥታዊ ሥርዓት ውክልናን በማረጋገጥ ብቻ የፖለቲካ መረጋጋት እና መግባባትን አያመጣም።

ብዝኃ ማንነትን በማሳሰብ ወደ መሐል እንዲመጡ በማድረግ ጭምር እንጂ" በማለት ነው የመደመር መንግሥት በገጽ 288 ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት መጠናከር የሚበጀውን መንገድ የሚያመላክተው።

የመደመር መንግሥት ከ2010 ዓ.ም ለውጥ በኋላ ሁሉንም አስተሳሰብ የሚያራምዱ የፖለቲካ ተዋናዮችን ለማሰባሰብ የሞከረውም ለዚህ እንደሆነ በመጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል፡፡

 

 

በለሚ ታደሰ