የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እያደረገው ያለውን ቅድመ ዝግጅት አጠናክሮ እንዲቀጥል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የቦርዱን የ2018 በጀት ዓመት የአንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት እና የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የቅድመ ዝግጅት አፈጻጸምን ገምግሟል።
በምክር ቤቱ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫው እያደረገ ያለው ቅድመ ዝግጅት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
የመራጮች እና የእጩዎች ምዝገባን ዲጂታል በሆነ መንገድ ለማከናወን የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ገልጸው፤ ጥቅም ላይ የሚውሉትን ቴክኖሎጂዎች ደኅንነትና ብቃት መፈተሽ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ቦርዱ ቀደም ሲል ከነበሩት ምርጫዎች ልምድ በመውሰድ የጀመራቸውን የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን በማጠናከር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራ አንደሞ በበኩላቸው፣ ቦርዱ ምርጫውን ስኬታማ ለማድረግ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አመላክተዋል።
ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ይሆን ዘንድ ምክር ቤቱ፣ መንግሥት እና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕግ እና በሕገ መንግሥት በተሰጧቸው ኃላፊነት መሠረት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ቋሚ ኮሚቴውም ለምርጫው ስኬት እያደረገ ያለውን ክትትልና ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አዝመራ ተናግረዋል።

የሲቪክ ማኅበራትን እና የሚዲያዎችን አቅም በመገንባት የዴሞክራሲ ልምምድ እንዲዳብር መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ የቦርዱን የሩብ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት እና የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን በዝርዝር ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።
በሪፖርቱም የምርጫ ጽሕፈት ቤቶችን የማደራጀትና በሰው ኃይል የማጠናከር ሥራ እንደተከናወነ ጠቁመዋል።
የተሟላ መሠረተ ልማት ያላቸው የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ላይ የዕጩ እና የመራጮች ምዝገባ በቴክኖሎጂ እንደሚታገዝ አመላክተዋል።
የመራጮች እና የእጩዎች ምዝገባን ቦርዱ በአዘጋጃቸው ሶፍትዌሮች በመታገዝ ለማከናወን ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ሙከራ በመላ ኢትዮጵያ እየሰፋ እንደሚሄድ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መሆኑን ማሳወቁ ይታወሳል።