Search

15 ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች ሕጋዊ ዕውቅና ሊያገኙ ነው

ረቡዕ ታኅሣሥ 01, 2018 69

በአማራ ክልል ሽምግልናን ጨምሮ 15 የሚሆኑ ባህላዊ የአለመግባባቶች መፍቻ ሥርዓቶች ሕጋዊ ዕውቅና ሊያገኙ መሆኑን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር በአካሄደው መድረክ የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና ዕውቅና ለመስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው፣ በክልሉ በተደረገ ጥናት መሠረት ሽምግልናን ጨምሮ 15 የሚሆኑ ባህላዊ የአለመግባባቶች መፍቻ ሥርዓቶች መኖራቸው ተረጋግጧል ብለዋል።
እነዚህ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች እውቅና እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል።
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሆነ የፍትሕ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ዘላቂ እርቅን በማስፈን ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸዋል።
በክልልሉ ለባህላዊ የፍርድ ቤቶች የሕግ ማዕቀፍ በመዘጋጀቱ፣ በቀጣይ ከሰብዓዊ መብቶች፣ ከሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም ከሕገ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በስተቀር ሌሎች የአለመግባባት ጉዳዮች በባህል ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲያገኙ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ለባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች ዕውቅና መስጠት የሚያስችል መመሪያ ተጠናቆ የትግበራ ዕቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ የሰው ኃይል ምልመላና ሥልጠና መጠናቀቁንም ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል።
 
በሳሙኤል ወርቃየሁ