Search

የፀረ ሙስና ትግሉ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራትን ማጠናከር ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ዓርብ ታኅሣሥ 03, 2018 29

ሙስናን የመከላከል ትግል መላው ማህበረሰብ ፣ ሁሉም ተቋማት በባለቤትነት ሊይዙት ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ዛሬ 22ኛውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀንን “ትውልድን በስነ-ምግባር፣ ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ሀሳብ ስናከብር ሙስናን ለመዋጋት ያለንን ቁርጠኝነት እና የገባነውን ቃል በማደስ ነው ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሙስናን የብልፅግናችን ፀር፣ የኢፍትሀዊነት ምንጭ በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳ አድርገን ያፋፋምነው ትግል ከዚህ ቀደም የነበረን አስከፊ መንግስታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት አስችሏል ሲሉም ገልጸዋል።
በዚህም እንደ ሀገር ብሎም እንደ ከተማ የህዝብና የመንግሥትን ሀብት በተገቢው የልማት ስራዎች ላይ በማዋላችን አስደናቂ የልማት ውጤቶች ማሳየት ችለናል ሲሉም ጠቁመዋል።
መንግሥታዊ/ስርዓታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት ብንችልም፣ በግለሰብ ደረጃ የሚታይ በመንግስት ሃላፊዎች እና ሰራተኞች የሚፈፀመው ሌብነት እና ጉቦኝነት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ለሙስና አጋላጭ አሰራሮችን ለመዝጋት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ሙስናን ከምንጩ ለማድረቅ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን በማጠናከር፣ መንግሥታዊ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆንና ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን በተሟላ መልክ ለመከላከል የሁሉንም ተቋማት ትግል እና የሁሉንም ሕብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ርብርብ ይጠበቃል ብለዋል።
ቤተሰብ፣ ማኅበረሰቡ፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት እና ሌሎችም ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ በፀረ-ሙስና ትግል ውስጥ በአመለካከትም በተግባርም ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በመሆኑም የፀረ-ሙስና ትግላችን ይበልጡን ውጤታማ እንዲሆን የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራትን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።