Search

‘ፋይዳ’ ለሌሎች ሀገሮች ያስገኘው ፋይዳ

ዓርብ ታኅሣሥ 03, 2018 91

በአውሮፓውያኑ 2024 በዓለም ዙሪያ 5 ቢሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ዲጂታል መታወቂያ እንደያዙ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ዜጎች ፈጣን፣ አስተማማኝ እና ፍትሐዊ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ በርካታ ሀገራት የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ደኅንነቱ የተረጋገጠ ልዩ መለያ በማቅረብ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለማግኘት እንዲሁም የሰነዶች ማጭበርበርን ለመከላከል የሚረዳው ዲጂታል መታወቂያ ቀልጣፋ ሥርዓት በመገንባት ረገድ ያለው ዓለም አቀፍ ተጠቃሚነት ምን ይመስላል የሚለውን ጥቂት እንመልከት።

የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትን በአፍሪካ እንደ ኢትዮጵያ (ፋይዳ)፣ ናይጄሪያ (ኤን አይ ኤን)፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ያሉ ሀገሮች የተሻለ የአገልግሎት ተደራሽነትን ለመፍጠር ጥቅም ላይ እያዋሉት ይገኛሉ። ይህም ሥርዓቱ በአፍሪካ እየተስፋፋ መምጣቱን ያመላክታል።

ኢስቶኒያ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽነትን በቀዳሚነት በመምራት የምትታወቅ ነች። ‘ኢ አይ ዲ’ ተብሎ የሚጠራው የኢስቶኒያ ዲጂታል መታወቂያ ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።

በሀገሪቱ ከ600 በላይ የሚሆኑ የመንግሥት የአገልግሎት ተቋማትን ከ24 ሺህ በላይ የግል ንግድ ድርጅቶች ጋር በማስተሳሰር አገልግሎት ይሰጣሉ።

በኢስቶኒያ የዲጂታል መታወቂያ ለዲጂታላይዝ ግብይት፣ በኦንላይን ምርጫ ለመሳተፍ፣ የጤና አገልግሎት ለማግኘት፣ የግብር ክፍያን ለመፈፀም እና የንግድ ምዝገባን ለማከናወን የሚያስችል አሠራርን ፈጥሯል። 

ይህን በማድረጓም ኢስቶኒያ 99 በመቶ የሚሆኑ ዜጎቿን የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት በማድረግ እየተጠቀመችበት ትገኛለች።

ይህም አሠራር ለሥራ ፈጣሪዎች እና ሥራቸውን ከሩቅ ሆነው ለሚሠሩ ሠራተኞች አዳዲስ የሥራ ዕድሎች መክፈት የቻለ ነው። ከዚህም ባሻገር የዲጂታል ፊርማ ልምምድን በማሳደግ ቀልጣፋ እና ጊዜ ቆጣቢ አሠራርን መፍጠር አስችሏል።

ሲንጋፖር ሌላኛዋ በዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚነት ለዓለም ምሳሌ የሆነች ሀገር ናት። በሀገሪቱ 97 በመቶ የሚሆነው ዜጋ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ነው።

የሲንጋፖር ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ደኅንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለማግኘትም ጭምር የሚረዳ ስለመሆኑ ይነገርለታል።

አገልግሎቱ ከ700 በላይ የመንግሥት የአገልግሎት ተቋማትን ከግል የንግድ ድርጅቶች ጋር በማስተሳሰር ዜጎች ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ አስችሏል።

ይህም ጠንካራ የሆነ የሕዝብ አመኔታን እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ አስችሏል። በዲጂታል መታወቂያ ዲጂታል ሰነዶችን መፈረም፣ የፋይናንስ ዕቅድ ማውጣት፣ በተለያዩ ኤጀንሲዎች ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ መረጃዎችን ለመሙላትም ያስችላል።

በቪዬትናም የዲጂታል መታወቂያ ልምድ በፍጥነት እያደገ የመጣ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2026 ሙሉ ለሙሉ ወይም መቶ በመቶ የዲጂታል አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አቅዳ እየሠራች ትገኛለች።

አሁን ላይ ሰማንያ በመቶ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ዲጂታላዝድ በሆነ መንገድ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

የዲጂታል መታወቂያ በመንግሥት የተሰጠ ሰነድ ወይም የዲጂታል መለያ ሲሆን በአንድ ሀገር ውስጥ የአንድን ግለሰብ መለያ ቁጥር በውስጡ ያካተተ በመሆኑ የአንድ ግለሰብ ማንነት እና ዜግነት ሕጋዊ ማረጋገጫ ሆኖም ያገለግላል።

በአጠቃላይ፣ የዲጂታል መታወቂያ የተቀላጠፉ ሥርዓቶችን በመዘርጋት የወረቀት ሥርዓቶችን አስወግዶ ዜጎች የመንግሥት አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ፣ ማንነታቸውን በቀላሉ እንዲያረጋግጡ ማድረግ ዓላማው አድርጎ እየሠራ ሲሆን በአንዳንድ ሀገራት ዲጂታላይዝ ግብይቶችን ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ እንዲፈፅሙ ያስችላል።

ኢትዮጵያም ይህንኑ ዓለም አቀፍ ልምድ በመቅሰም ዲጂታል መታወቂያን ተግባራዊ በማድረግ ተደራሽ እያደረገች ነው።

በዚህም አገልግሎቶችን በዲጂታል መታወቂያ አማካኝነት ለመስጠት ሰፊ ሥራ በማከናወን ላይ ትገኛለች።

 

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

#EBC #ebcdotstream #Ethiopai #DigitalEthiopia #Fayda #DigitalID